John 11:1-16:33

Amharic(i) 1 ከማርያምና ከእኅትዋ ከማርታ መንደር ከቢታንያ የሆነ አልዓዛር የሚባል አንድ ሰው ታሞ ነበር። 2 ማርያምም ጌታን ሽቱ የቀባችው እግሩንም በጠጕርዋ ያበሰችው ነበረች፤ ወንድምዋም አልዓዛር ታሞ ነበር። 3 ስለዚህ እኅቶቹ ጌታ ሆይ፥ እነሆ የምትወደው ታሞአል ብለው ወደ እርሱ ላኩ። 4 ኢየሱስም ሰምቶ። ይህ ህመም የእግዚአብሔር ልጅ በእርሱ ይከብር ዘንድ ስለ እግዚአብሔር ክብር ነው እንጂ ለሞት አይደለም አለ። 5 ኢየሱስም ማርታንና እኅትዋን አልዓዛርንም ይወድ ነበር። 6 እንደ ታመመም በሰማ ጊዜ ያን ጊዜ በነበረበት ስፍራ ሁለት ቀን ዋለ፤ 7 ከዚህም በኋላ ለደቀ መዛሙርቱ። ወደ ይሁዳ ደግሞ እንሂድ አላቸው። 8 ደቀ መዛሙርቱ። መምህር ሆይ፥ አይሁድ ከጥቂት ጊዜ በፊት ሊወግሩህ ይፈልጉ ነበር፥ ደግሞም ወደዚያ ትሄዳለህን? አሉት። 9 ኢየሱስም መልሶ። ቀኑ አሥራ ሁለት ሰዓት አይደለምን? በቀን የሚመላለስ ቢኖር የዚህን ዓለም ብርሃን ያያልና አይሰናከልም፤ 10 በሌሊት የሚመላለስ ቢኖር ግን ብርሃን በእርሱ ስለ ሌለ ይሰናከላል አላቸው። 11 ይህን ተናገረ፤ ከዚህም በኋላ። ወዳጃችን አልዓዛር ተኝቶአል፤ ነገር ግን ከእንቅልፉ ላስነሣው እሄዳለሁ አላቸው። 12 እንግዲህ ደቀ መዛሙርቱ። ጌታ ሆይ፥ ተኝቶስ እንደ ሆነ ይድናል አሉት። 13 ኢየሱስስ ስለ ሞቱ ተናግሮ ነበር፤ እነርሱ ግን ስለ እንቅልፍ መተኛት እንደ ተናገረ መሰላቸው። 14 እንግዲህ ያን ጊዜ ኢየሱስ በግልጥ። አልዓዛር ሞተ፤ 15 እንድታምኑም በዚያ ባለመኖሬ ስለ እናንተ ደስ ይለኛል፤ ነገር ግን ወደ እርሱ እንሂድ አላቸው። 16 ስለዚህ ዲዲሞስ የሚሉት ቶማስ ለባልንጀሮቹ ለደቀ መዛሙርት። ከእርሱ ጋር እንሞት ዘንድ እኛ ደግሞ እንሂድ አለ። 17 ኢየሱስም በመጣ ጊዜ በመቃብር እስከ አሁን አራት ቀን ሆኖት አገኘው። 18 ቢታንያም አሥራ አምስት ምዕራፍ ያህል ለኢየሩሳሌም ቅርብ ነበረች። 19 ከአይሁድም ብዙዎች ስለ ወንድማቸው ሊያጽናኑአቸው ወደ ማርታና ወደ ማርያም መጥተው ነበር። 20 ማርታም ኢየሱስ እንደ መጣ በሰማች ጊዜ ልትቀበለው ወጣች፤ ማርያም ግን በቤት ተቀምጣ ነበር። 21 ማርታም ኢየሱስን። ጌታ ሆይ፥ አንተ በዚህ ኖረህ ብትሆን ወንድሜ ባልሞተም ነበር፤ 22 አሁንም ከእግዚአብሔር የምትለምነውን ሁሉ እግዚአብሔር እንዲሰጥህ አውቃለሁ አለችው። 23 ኢየሱስም። ወንድምሽ ይነሣል አላት። 24 ማርታም። በመጨረሻው ቀን በትንሣኤ እንዲነሣ አውቃለሁ አለችው። 25 ኢየሱስም። ትንሣኤና ሕይወት እኔ ነኝ፤ የሚያምንብኝ ቢሞት እንኳ ሕያው ይሆናል፤ 26 ሕያው የሆነም የሚያምንብኝም ሁሉ ለዘላለም አይሞትም፤ ይህን ታምኚያለሽን? አላት። 27 እርስዋም። አዎን ጌታ ሆይ፤ አንተ ወደ ዓለም የሚመጣው ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ እንደ ሆንህ እኔ አምናለሁ አለችው። 28 ይህንም ብላ ሄደች እኅትዋንም ማርያምን በስውር ጠርታ። መምህሩ መጥቶአል ይጠራሽማል አለቻት። 29 እርስዋም በሰማች ጊዜ ፈጥና ተነሣች ወደ እርሱም መጣች፤ 30 ኢየሱስም ማርታ በተቀበለችበት ስፍራ ነበረ እንጂ ገና ወደ መንደሩ አልገባም ነበር። 31 ሲያጽናኑአት ከእርስዋ ጋር በቤት የነበሩ አይሁድም ማርያም ፈጥና እንደ ተነሣችና እንደ ወጣች ባዩ ጊዜ፥ ወደ መቃብር ሄዳ በዚያ ልታለቅስ መስሎአቸው ተከተሉአት። 32 ማርያምም ኢየሱስ ወዳለበት መጥታ ባየችው ጊዜ በእግሩ ላይ ወድቃ። ጌታ ሆይ፥ አንተ በዚህ ኖረህ ብትሆን ወንድሜ ባልሞተም ነበር አለችው። 33 ኢየሱስም እርስዋ ስታለቅስ ከእርስዋም ጋር የመጡት አይሁድ ሲያለቅሱ አይቶ በመንፈሱ አዘነ በራሱም ታወከ፤ 34 ወዴት አኖራችሁት? አለም። እነርሱም። ጌታ ሆይ፥ መጥተህ እይ አሉት። 35 ኢየሱስም እንባውን አፈሰሰ። 36 ስለዚህ አይሁድ። እንዴት ይወደው እንደ ነበረ እዩ አሉ። 37 ከእነርሱ ግን አንዳንዶቹ። ይህ የዕውሩን ዓይኖች የከፈተ ይህን ደግሞ እንዳይሞት ያደርግ ዘንድ ባልቻለም ነበርን? አሉ። 38 ኢየሱስም በራሱ አዝኖ ወደ መቃብሩ መጣ፤ እርሱም ዋሻ ነበረ፤ ድንጋይም ተገጥሞበት ነበር። 39 ኢየሱስ። ድንጋዩን አንሡ አለ። የሞተውም እኅት ማርታ። ጌታ ሆይ፥ ከሞተ አራት ቀን ሆኖታልና አሁን ይሸታል አለችው። 40 ኢየሱስ። ብታምኚስ የእግዚአብሔርን ክብር እንድታዪ አልነገርሁሽምን? አላት። 41 ድንጋዩንም አነሡት። ኢየሱስም ዓይኖቹን ወደ ላይ አንሥቶ። አባት ሆይ፥ ስለ ሰማኸኝ አመሰግንሃለሁ። 42 ሁልጊዜም እንድትሰማኝ አወቅሁ፤ ነገር ግን አንተ እንደ ላክኸኝ ያምኑ ዘንድ በዚህ ዙሪያ ስለ ቆሙት ሕዝብ ተናገርሁ አለ። 43 ይህንም ብሎ በታላቅ ድምፅ። አልዓዛር ሆይ፥ ወደ ውጭ ና ብሎ ጮኸ። 44 የሞተውም እጆቹና እግሮቹ በመግነዝ እንደ ተገነዙ ወጣ፤ ፈቱም በጨርቅ እንደ ተጠመጠመ ነበር። ኢየሱስም። ፍቱትና ይሂድ ተዉት አላቸው። 45 ስለዚህ ወደ ማርያም ከመጡት፥ ኢየሱስም ያደረገውን ካዩት ከአይሁድ ብዙዎች በእርሱ አመኑ፤ 46 ከእነርሱ አንዳንዶቹ ግን ወደ ፈሪሳውያን ሄደው ኢየሱስ ያደረገውን ነገሩአቸው። 47 እንግዲህ የካህናት አለቆችና ፈሪሳውያን ሸንጎ ሰብስበው። ምን እናድርግ? ይህ ሰው ብዙ ምልክቶች ያደርጋልና። 48 እንዲሁ ብንተወው ሁሉ በእርሱ ያምናሉ፤ የሮሜም ሰዎች መጥተው አገራችንን ወገናችንንም ይወስዳሉ አሉ። 49 በዚያችም ዓመት ሊቀ ካህናት የነበረ ቀያፋ የሚሉት ከእነርሱ አንዱ። እናንተ ምንም አታውቁም፤ 50 ሕዝቡም ሁሉ ከሚጠፋ አንድ ሰው ስለ ሕዝቡ ይሞት ዘንድ እንዲሻለን አታስቡም አላቸው። 51 ይህንም የተናገረ ከራሱ አይደለም፥ ነገር ግን በዚያች ዓመት ሊቀ ካህናት ነበረና ኢየሱስ ስለ ሕዝቡ ሊሞት እንዳለው ትንቢት ተናገረ፤ 52 ስለ ሕዝቡም ሁሉ አይደለም፥ ነገር ግን የተበተኑትን የእግዚአብሔርን ልጆች ደግሞ በአንድነት እንዲሰበስባቸው ነው እንጂ። 53 እንግዲህ ከዚያ ቀን ጀምረው ሊገድሉት ተማከሩ። 54 ከዚያ ወዲያም ኢየሱስ በአይሁድ መካከል ተገልጦ አልተመላለሰም፤ ነገር ግን ከዚያ በምድረ በዳ አጠገብ ወዳለች ምድር፥ ኤፍሬም ወደምትባል ከተማ ሄደ፤ በዚያም ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ተቀመጠ። 55 የአይሁድም ፋሲካ ቀርቦ ነበር። ብዙ ሰዎችም ራሳቸውን ያነጹ ዘንድ ከፋሲካ በፊት ከአገሩ ወደ ኢየሩሳሌም ወጡ። 56 ኢየሱስንም ይፈልጉት ነበር፤ በመቅደስም ቆመው እርስ በርሳቸው። ምን ይመስላችኋል? ወደ በዓሉ አይመጣም ይሆንን? ተባባሉ። 57 የካህናት አለቆችም ፈሪሳውያንም ይይዙት ዘንድ እርሱ ያለበትን ስፍራ የሚያውቀው ሰው ቢኖር እንዲያመለክታቸው አዘው ነበር።12 1 ከፋሲካም በፊት በስድስተኛው ቀን ኢየሱስ ከሙታን ያስነሣው አልዓዛር ወደ ነበረበት ወደ ቢታንያ መጣ። 2 በዚያም እራት አደረጉለት፤ ማርታም ታገለግል ነበር፤ አልዓዛር ግን ከእርሱ ጋር ከተቀመጡት አንዱ ነበረ። 3 ማርያምም ዋጋው እጅግ የከበረ የጥሩ ናርዶስ ሽቱ ንጥር ወስዳ የኢየሱስን እግር ቀባች፤ በጠጕርዋም እግሩን አበሰች፤ ቤቱም ከናርዶስ ሽቱ ሞላ። 4 ነገር ግን ከደቀ መዛሙርቱ አንዱ አሳልፎ ሊሰጠው ያለው የስምዖን ልጅ የአስቆሮቱ ይሁዳ። 5 ይህ ሽቱ ለሦስት መቶ ዲናር ተሽጦ ለድሆች ያልተሰጠ ስለ ምን ነው? አለ። 6 ይህንም የተናገረ ሌባ ስለ ነበረ ነው እንጂ ለድሆች ተገድዶላቸው አይደለም፤ ከረጢትም ይዞ በውስጡ ከሚገባው ይወስድ ስለ ነበረ ነው። 7 ኢየሱስም። ለምቀበርበት ቀን እንድትጠብቀው ተውአት፤ 8 ድሆችስ ሁልጊዜ ከእናንተ ጋር ይኖራሉና፥ እኔ ግን ሁልጊዜ ከእናንተ ጋር አልኖርም አለ። 9 ከአይሁድም ብዙ ሕዝብ በዚያ እንደ ነበረ አውቀው መጡ፥ ከሙታንም ያስነሣውን አልዓዛርን ደግሞ እንዲያዩ ነበረ እንጂ ስለ ኢየሱስ ብቻ አይደለም። 10 የካህናት አለቆችም አልዓዛርን ደግሞ ሊገድሉት ተማከሩ፥ 11 ከአይሁድ ብዙዎች ከእርሱ የተነሣ ሄደው በኢየሱስ ያምኑ ነበርና። 12 በማግሥቱ ወደ በዓሉ መጥተው የነበሩ ብዙ ሕዝብ ኢየሱስ ወደ ኢየሩሳሌም እንዲመጣ በሰሙ ጊዜ፥ 13 የዘንባባ ዛፍ ዝንጣፊ ይዘው ሊቀበሉት ወጡና። ሆሣዕና፤ በጌታ ስም የሚመጣ የእስራኤል ንጉሥ የተባረከ ነው እያሉ ጮኹ። 14 አንቺ የጽዮን ልጅ አትፍሪ፤ እነሆ፥ ንጉሥሽ በአህያ ውርንጫ ላይ ተቀምጦ ይመጣል ተብሎ እንደ ተጻፈ፥ ኢየሱስ የአህያ ውርንጫ አግኝቶ በእርሱ ተቀመጠ። 16 ደቀ መዛሙርቱም ይህን ነገር በመጀመሪያ አላስተዋሉም፤ ነገር ግን ኢየሱስ ከከበረ በኋላ በዚያን ጊዜ ይህ ስለ እርሱ እንደ ተጻፈ ይህንም እንዳደረጉለት ትዝ አላቸው። 17 አልዓዛርንም ከመቃብር ጠርቶ ከሙታን ሲያስነሣው ከእርሱ ጋር የነበሩት ሕዝብ ይመሰክሩለት ነበር። 18 ስለዚህ ደግሞ ሕዝቡ ይህን ምልክት እንዳደረገ ስለ ሰሙ ሊቀበሉት ወጡ። 19 ሰለዚህ ፈሪሳውያን እርስ በርሳቸው። አንድ ስንኳ ልታደርጉ እንዳይቻላችሁ ታያላችሁን? እነሆ፥ ዓለሙ በኋላው ተከትሎት ሄዶአል ተባባሉ። 20 በበዓሉም ሊሰግዱ ከወጡት አንዳንዶቹ የግሪክ ሰዎች ነበሩ፤ 21 እነርሱም ከገሊላ ቤተ ሳይዳ ወደሚሆን ወደ ፊልጶስ መጥተው። ጌታ ሆይ፥ ኢየሱስን ልናይ እንወዳለን ብለው ለመኑት። 22 ፊልጶስም መጥቶ ለእንድርያስ ነገረው፤ እንድርያስና ፊልጶስ መጥተው ለኢየሱስ ነገሩት። 23 ኢየሱስም መለሰላቸው፥ እንዲህ ሲል። የሰው ልጅ ይከብር ዘንድ ሰዓቱ ደርሶአል። 24 እውነት እውነት እላችኋለሁ፥ የስንዴ ቅንጣት በምድር ወድቃ ካልሞተች ብቻዋን ትቀራለች፤ ብትሞት ግን ብዙ ፍሬ ታፈራለች። 25 ነፍሱን የሚወድ ያጠፋታል፥ ነፍሱንም በዚህ ዓለም የሚጠላ ለዘላለም ሕይወት ይጠብቃታል። 26 የሚያገለግለኝ ቢኖር ይከተለኝ፥ እኔም ባለሁበት አገልጋዬ ደግሞ በዚያ ይሆናል፤ የሚያገለግለኝም ቢኖር አብ ያከብረዋል። 27 አሁን ነፍሴ ታውካለች ምንስ እላለሁ? አባት ሆይ፥ ከዚህ ሰዓት አድነኝ። ነገር ግን ስለዚህ ወደዚህ ሰዓት መጣሁ። 28 አባት ሆይ፥ ስምህን አክብረው። ስለዚህም። አከበርሁት ደግሞም አከብረዋለሁ የሚል ድምፅ ከሰማይ መጣ። 29 በዚያ ቆመው የነበሩትም ሕዝብ በሰሙ ጊዜ። ነጐድጓድ ነው አሉ፤ ሌሎች። መልአክ ተናገረው አሉ። 30 ኢየሱስም መለሰ፥ እንዲህ ሲል። ይህ ድምፅ ስለ እናንተ መጥቶአል እጂ ስለ እኔ አይደለም። 31 አሁን የዚህ ዓለም ፍርድ ደርሶአል፤ አሁን የዚህ ዓለም ገዥ ወደ ውጭ ይጣላል፤ 32 እኔም ከምድር ከፍ ከፍ ያልሁ እንደ ሆነ ሁሉን ወደ እኔ እስባለሁ። 33 በምን ዓይነትም ሞት ይሞት ዘንድ እንዳለው ሲያመለክታቸው ይህን ተናገረ። 34 እንግዲህ ሕዝቡ። እኛስ ክርስቶስ ለዘላለም እንዲኖር ከሕጉ ሰምተናል፤ አንተስ የሰው ልጅ ከፍ ከፍ ይል ዘንድ እንዲያስፈልገው እንዴት ትላላህ? ይህ የሰው ልጅ ማን ነው? ብለው መለሱለት። 35 ኢየሱስም። ገና ጥቂት ጊዜ ብርሃን ከእናንተ ጋር ነው። ጨለማ እንዳይደርስባችሁ ብርሃን ሳለላችሁ ተመላለሱ፤ በጨለማም የሚመላለስ ወዴት እንዲሄድ አያውቅም። 36 የብርሃን ልጆች እንድትሆኑ ብርሃን ሳለላችሁ በብርሃኑ እመኑ አላቸው። ኢየሱስም ይህን ተናግሮ ሄደና ተሰወረባቸው። 37 ነገር ግን ይህን ያህል ምልክት በፊታቸው ምንም ቢያደርግ፤ ነቢዩ ኢሳይያስ። ጌታ ሆይ፥ ማን ምስክርነታችንን አመነ? የእግዚአብሔርስ ክንድ ለማን ተገለጠ? ብሎ የተናገረው ቃል ይፈጸም ዘንድ በእርሱ አላመኑም። 39 ኢሳይያስ ደግሞ። በዓይኖቻቸው እንዳያዩ፥ በልባቸውም እንዳያስተውሉ፥ እንዳይመለሱም፥ እኔም እንዳልፈውሳቸው፥ ዓይኖቻቸውን አሳወረ ልባቸውንም አደነደነ ብሎአልና ስለዚህ ማመን አቃታቸው። 41 ክብሩን ስለ አየ ኢሳይያስ ይህን አለ፥ ስለ እርሱም ተናገረ። 42 ከዚህም ጋር ከአለቆች ደግሞ ብዙዎች በእርሱ አመኑ፤ ነገር ግን ከምኵራብ እንዳያስወጡአቸው በፈሪሳውያን ምክንያት አልመሰከሩለትም፤ 43 ከእግዚአብሔር ክብር ይልቅ የሰውን ክብር ወደዋልና። 44 ኢየሱስም ጮኸ፥ እንዲህም አለ። በእኔ የሚያምን በላከኝ ማመኑ ነው እንጂ በእኔ አይደለም፤ 45 እኔንም የሚያይ የላከኝን ያያል። 46 በእኔ የሚያምን ሁሉ በጨለማ እንዳይኖር እኔ ብርሃን ሆኜ ወደ ዓለም መጥቻለሁ። 47 ዓለምን ላድን እንጂ በዓለም ልፈርድ አልመጣሁምና ቃሌን ሰምቶ የማይጠብቀው ቢኖር የምፈርድበት እኔ አይደለሁም። 48 የሚጥለኝ ቃሌንም የማይቀበለው እርሱ የሚፈርድበት አለው፤ እኔ የተናገርሁት ቃል እርሱ በመጨረሻው ቀን ይፈርድበታል። 49 እኔ ከራሴ አልተናገርሁምና፤ ነገር ግን የላከኝ አብ እርሱ የምለውን የምናገረውንም ትእዛዝ ሰጠኝ። 50 ትእዛዙም የዘላለም ሕይወት እንደ ሆነች አውቃለሁ። ስለዚህ እኔ የምናገረውን አብ እንደ ነገረኝ እንዲሁ እናገራለሁ።13 1 ኢየሱስም ከፋሲካ በዓል በፊት፥ ከዚህ ዓለም ወደ አብ የሚሄድበት ሰዓት እንደ ደረሰ አውቆ፥ በዚህ ዓለም ያሉትን ወገኖቹን የወደዳቸውን እስከ መጨረሻ ወደዳቸው። 2 እራትም ሲበሉ ዲያብሎስ በስምዖን ልጅ በአስቆሮቱ በይሁዳ ልብ አሳልፎ እንዲሰጠው አሳብ ካገባ በኋላ፥ 3 ኢየሱስ አብ ሁሉን በልጁ እንደ ሰጠው ከእግዚአብሔርም እንደ ወጣ ወደ እግዚአብሔርም እንዲሄድ አውቆ፥ 4 ከእራት ተነሣ ልብሱንም አኖረ፥ ማበሻም ጨርቅ ወስዶ ታጠቀ፤ 5 በኋላም በመታጠቢያው ውኃ ጨመረ፥ የደቀ መዛሙርቱንም እግር ሊያጥብና በታጠቀበትም ማበሻ ጨርቅ ሊያብስ ጀመረ። 6 ወደ ስምዖን ጴጥሮስም መጣ፤ እርሱም። ጌታ ሆይ፥ አንተ የእኔን እግር ታጥባለህን? አለው። 7 ኢየሱስም መልሶ። እኔ የማደርገውን አንተ አሁን አታውቅም፥ በኋላ ግን ታስተውለዋለህ አለው። 8 ጴጥሮስም። የእኔን እግር ለዘላለም አታጥብም አለው። ኢየሱስም። ካላጠብሁህ፥ ከእኔ ጋር ዕድል የለህም ብሎ መለሰለት። 9 ስምዖን ጴጥሮስም። ጌታ ሆይ፥ እጄንና ራሴን ደግሞ እንጂ እግሬን ብቻ አይደለም አለው። 10 ኢየሱስም። የታጠበ እግሩን ከመታጠብ በቀር ሌላ አያስፈልገውም፥ ሁለንተናው ግን ንጹሕ ነው፤ እናንተም ንጹሐን ናችሁ፥ ነገር ግን ሁላችሁ አይደላችሁም አለው። 11 አሳልፎ የሚሰጠውን ያውቅ ነበርና፤ ስለዚህ። ሁላችሁ ንጹሐን አይደላችሁም አለው። 12 እግራቸውንም አጥቦ ልብሱንም አንሥቶ ዳግመኛ ተቀመጠ፥ እንዲህም አላቸው። ያደረግሁላችሁን ታስተውላላችሁን? 13 እናንተ መምህርና ጌታ ትሉኛላችሁ፤ እንዲሁ ነኝና መልካም ትላላችሁ። 14 እንግዲህ እኔ ጌታና መምህር ስሆን እግራችሁን ካጠብሁ፥ እናንተ ደግሞ እርስ በርሳችሁ እግራችሁን ትተጣጠቡ ዘንድ ይገባችኋል። 15 እኔ ለእናንተ እንዳደረግሁ እናንተ ደግሞ ታደርጉ ዘንድ ምሳሌ ሰጥቻችኋለሁና። 16 እውነት እውነት እላችኋለሁ፥ ባሪያ ከጌታው አይበልጥም። መልእክተኛም ከላከው አይበልጥም። 17 ይህን ብታውቁ፥ ብታደርጉትም ብፁዓን ናችሁ። 18 ስለ ሁላችሁ አልናገርም፤ እኔ የመረጥኋቸውን አውቃለሁ፤ ነገር ግን መጽሐፍ። እንጀራዬን የሚበላ በእኔ ላይ ተረከዙን አነሣብኝ ያለው ይፈጸም ዘንድ ነው። 19 በሆነ ጊዜ እኔ እንደ ሆንሁ ታምኑ ዘንድ፥ ከአሁን ጀምሬ አስቀድሞ ሳይሆን እነግራችኋለሁ። 20 እውነት እውነት እላችኋለሁ፥ ማናቸውን የምልከውን የሚቀበል እኔን ይቀበላል፥ እኔንም የሚቀበል የላከኝን ይቀበላል። 21 ኢየሱስ ይህን ብሎ በመንፈሱ ታወከ መስክሮም። እውነት እውነት እላችኋለሁ፥ ከእናንተ አንዱ አሳልፎ ይሰጠኛል አለ። 22 ደቀ መዛሙርቱ ስለ ማን እንደ ተናገረ አመንትተው እርስ በርሳቸው ተያዩ። 23 ኢየሱስም ይወደው የነበረ ከደቀ መዛሙርቱ አንዱ በኢየሱስ ደረት ላይ ተጠጋ፤ 24 ስለዚህ ስምዖን ጴጥሮስ እርሱን ጠቅሶ። ስለማን እንደ ተናገረ ንገረን አለው። 25 እርሱም በኢየሱስ ደረት እንዲህ ተጠግቶ። ጌታ ሆይ፥ ማን ነው? አለው። 26 ኢየሱስም። እኔ ቍራሽ አጥቅሼ የምሰጠው እርሱ ነው ብሎ መለሰለት። ቍራሽም አጥቅሶ ለአስቆሮቱ ለስምዖን ልጅ ለይሁዳ ሰጠው። 27 ቍራሽም ከተቀበለ በኋላ ያን ጊዜ ሰይጣን ገባበት። እንግዲህ ኢየሱስ። የምታደርገውን ቶሎ ብለህ አድርግ አለው። 28 ነገር ግን ከተቀመጡት ስለ ምን ይህን እንዳለው ማንም አላወቀም፤ 29 ይሁዳ ከረጢቱን የያዘ ስለ ሆነ፥ ኢየሱስ። ለበዓሉ የሚያስፈልገንን ግዛ፥ ወይም ለድሆች ምጽዋት እንዲሰጥ ያለው ለአንዳንዱ መስሎአቸው ነበርና። 30 እርሱም ቍራሹን ከተቀበለ በኋላ ወዲያው ወጣ፤ ሌሊትም ነበረ። 31 ከወጣም በኋላ ኢየሱስ እንዲ አለ። አሁን የሰው ልጅ ከበረ እግዚአብሔርም ሰለ እርሱ ከበረ፤ 32 እግዚአብሔር ስለ እርሱ የከበረ ከሆነ፥ እግዚአብሔር ደግሞ እርሱን ራሱን ያከብረዋል ወዲያውም ያከብረዋል። 33 ልጆች ሆይ፥ ገና ጥቂት ጊዜ ከእናንተ ጋር ነኝ፤ ትፈልጉኛላችሁ፤ ለአይሁድም። እኔ ወደምሄድበት እናንተ ልትመጡ አይቻላችሁም እንዳልኋቸው፥ አሁን ለእናንተ ደግሞ እላችኋለሁ። 34 እርስ በርሳችሁ ትዋደዱ ዘንድ፥ እንደ ወደድኋችሁ እናንተ ደግሞ እርስ በርሳችሁ ትዋደዱ ዘንድ አዲስ ትእዛዝ እሰጣችኋለሁ። 35 እርስ በርሳችሁ ፍቅር ቢኖራችሁ፥ ደቀ መዛሙርቴ እንደ ሆናችሁ ሰዎች ሁሉ በዚህ ያውቃሉ። 36 ስምዖን ጴጥሮስም። ጌታ ሆይ፥ ወዴት ትሄዳለህ? አለው። ኢየሱስም። ወደምሄድበት አሁን ልትከተለኝ አትችልም፥ ነገር ግን በኋላ ትከተለኛለህ ብሎ መለሰለት። 37 ጴጥሮስም። ጌታ ሆይ፥ አሁን ልከተልህ አለመቻሌ ስለ ምንድር ነው? ነፍሴን ስንኳ ስለ አንተ እሰጣለሁ አለው። 38 ኢየሱስም እንዲህ ብሎ መለሰለት። ነፍስህን ስለ እኔ ትሰጣለህን? እውነት እውነት እልሃለሁ፥ ሦስት ጊዜ እስክትክደኝ ድረስ ዶሮ አይጮኽም።14 1 ልባችሁ አይታወክ፤ በእግዚአብሔር እመኑ፥ በእኔም ደግሞ እመኑ። 2 በአባቴ ቤት ብዙ መኖሪያ አለ፤ እንዲህስ ባይሆን ባልኋችሁ ነበር፤ ስፍራ አዘጋጅላችሁ ዘንድ እሄዳለሁና፤ 3 ሄጄም ስፍራ ባዘጋጅላችሁ፥ እኔ ባለሁበት እናንተ ደግሞ እንድትሆኑ ሁለተኛ እመጣለሁ ወደ እኔም እወስዳችኋለሁ። 4 ወደምሄድበትም ታውቃላችሁ፥ መንገዱንም ታውቃላችሁ። 5 ቶማስም። ጌታ ሆይ፥ ወደምትሄድበት አናውቅም፤ እንዴትስ መንገዱን እናውቃለን? አለው። 6 ኢየሱስም። እኔ መንገድና እውነት ሕይወትም ነኝ፤ በእኔ በቀር ወደ አብ የሚመጣ የለም። 7 እኔንስ ብታውቁኝ አባቴን ደግሞ ባወቃችሁ ነበር። ከአሁንም ጀምራችሁ ታውቁታላችሁ አይታችሁትማል አለው። 8 ፊልጶስ። ጌታ ሆይ፥ አብን አሳየንና ይበቃናል አለው። 9 ኢየሱስም አለው። አንተ ፊልጶስ፥ ይህን ያህል ዘመን ከእናንተ ጋር ስኖር አታውቀኝምን? እኔን ያየ አብን አይቶአል፤ እንዴትስ አንተ። አብን አሳየን ትላለህ? 10 እኔ በአብ እንዳለሁ አብም በእኔ እንዳለ አታምንምን? እኔ የምነግራችሁን ቃል ከራሴ አልናገረውም፤ ነገር ግን በእኔ የሚኖረው አብ እርሱ ሥራውን ይሠራል። 11 እኔ በአብ እንዳለሁ አብም በእኔ እንዳለ እመኑኝ፤ ባይሆንስ ስለ ራሱ ስለ ሥራው እመኑኝ። 12 እውነት እውነት እላችኋለሁ፥ በእኔ የሚያምን እኔ የማደርገውን ሥራ እርሱ ደግሞ ያደርጋል፤ ከዚህም የሚበልጥ ያደርጋል፥ 13 እኔ ወደ አብ እሄዳለሁና፤ አብም ስለ ወልድ እንዲከበር በስሜ የምትለምኑትን ሁሉ አደርገዋለሁ። 14 ማናቸውንም ነገር በስሜ ብትለምኑ እኔ አደርገዋለሁ። 15 ብትወዱኝ ትእዛዜን ጠብቁ። እኔም አብን እለምናለሁ ለዘላለምም ከእናንተ ጋር እንዲኖር ሌላ አጽናኝ ይሰጣችኋል፤ 17 እርሱም ዓለም የማያየውና የማያውቀው ስለ ሆነ ሊቀበለው የማይቻለው የእውነት መንፈስ ነው፤ ነገር ግን ከእናንተ ዘንድ ስለሚኖር በውሥጣችሁም ስለሚሆን እናንተ ታውቃላችሁ። 18 ወላጆች እንደ ሌላቸው ልጆች አልተዋችሁም፤ ወደ እናንተ እመጣለሁ። 19 ገና ጥቂት ዘመን አለ ከዚህም በኋላ ዓለም አያየኝም፤ እናንተ ግን ታዩኛላችሁ፤ እኔ ሕያው ነኝና እናንተ ደግሞ ሕያዋን ትሆናላችሁ። 20 እኔ በአባቴ እንዳለሁ እናንተም በእኔ እንዳላችሁ እኔም በእናንተ እንዳለሁ በዚያን ቀን ታውቃላችሁ። 21 ትእዛዜ በእርሱ ዘንድ ያለችው የሚጠብቃትም የሚወደኝ እርሱ ነው፤ የሚወደኝንም አባቴ ይወደዋል እኔም እወደዋለሁ ራሴንም እገልጥለታለሁ። 22 የአስቆሮቱ ያይደለ ይሁዳ። ጌታ ሆይ፥ ለዓለም ሳይሆን ራስህን ለእኛ ልትገልጥ ያለህ እንዴት ነው? አለው። 23 ኢየሱስም መለሰ አለውም። የሚወደኝ ቢኖር ቃሌን ይጠብቃል፤ አባቴም ይወደዋል ወደ እርሱም እንመጣለን በእርሱም ዘንድ መኖሪያ እናደርጋለን። 24 የማይወደኝ ቃሌን አይጠብቅም፤ የምትሰሙትም ቃል የላከኝ የአብ ነው እንጂ የእኔ አይደለም። 25 ከእናንተ ዘንድ ስኖር ይህን ነግሬአችኋለሁ፤ 26 አብ በስሜ የሚልከው ግን መንፈስ ቅዱስ የሆነው አጽናኝ እርሱ ሁሉን ያስተምራችኋል እኔም የነገርኋችሁን ሁሉ ያሳስባችኋል። 27 ሰላምን እተውላችኋለሁ፥ ሰላሜን እሰጣችኋለሁ፤ እኔ የምሰጣችሁ ዓለም እንደሚሰጥ አይደለም። ልባችሁ አይታወክ አይፍራም። 28 እኔ እሄዳለሁ ወደ እናንተም እመጣለሁ እንዳልኋችሁ ሰማችሁ። የምትወዱኝስ ብትሆኑ ከእኔ አብ ይበልጣልና ወደ አብ በመሄዴ ደስ ባላችሁ ነበር። 29 ከሆነም በኋላ ታምኑ ዘንድ አሁን አስቀድሞ ሳይሆን። ነግሬአችኋለሁ። 30 ከእንግዲህ ወዲህ ከእናንተ ጋር ብዙ አልናገርም፥ የዚህ ዓለም ገዥ ይመጣልና፤ በእኔ ላይም አንዳች የለውም፤ 31 ነገር ግን አብን እንድወድ ዓለም ሊያውቅ፥ አብም እንዳዘዘኝ፥ እንዲሁ አደርጋለሁ። ተነሡ፤ ከዚህ እንሂድ።15 1 እውነተኛ የወይን ግንድ እኔ ነኝ፤ ገበሬውም አባቴ ነው። 2 ፍሬ የማያፈራውን በእኔ ያለውን ቅርንጫፍ ሁሉ ያስወግደዋል፤ ፍሬ የሚያፈራውንም ሁሉ አብዝቶ እንዲያፈራ ያጠራዋል። 3 እናንተ ስለ ነገርኋችሁ ቃል አሁን ንጹሐን ናችሁ፤ 4 በእኔ ኑሩ እኔም በእናንተ። ቅርንጫፍ በወይኑ ግንድ ባይኖር ከራሱ ፍሬ ሊያፈራ እንዳይቻለው፥ እንዲሁ እናንተ ደግሞ በእኔ ባትኖሩ አትችሉም። 5 እኔ የወይን ግንድ ነኝ እናንተም ቅርንጫፎች ናችሁ። ያለ እኔ ምንም ልታደርጉ አትችሉምና በእኔ የሚኖር እኔም በእርሱ፥ እርሱ ብዙ ፍሬ ያፈራል። 6 በእኔ የማይኖር ቢሆን እንደ ቅርንጫፍ ወደ ውጭ ይጣላል ይደርቅማል፤ እነርሱንም ሰብስበው ወደ እሳት ይጥሉአቸዋል፥ ያቃጥሉአቸውማል። 7 በእኔ ብትኖሩ ቃሎቼም በእናንተ ቢኖሩ የምትወዱትን ሁሉ ለምኑ ይሆንላችሁማል። 8 ብዙ ፍሬ ብታፈሩና ደቀ መዛሙርቴ ብትሆኑ በዚህ አባቴ ይከበራል። 9 አብ እንደ ወደደኝ እኔ ደግሞ ወደድኋችሁ፤ በፍቅሬ ኑሩ። 10 እኔ የአባቴን ትእዛዝ እንደ ጠበቅሁ በፍቅሩም እንደምኖር፥ ትእዛዜን ብትጠብቁ በፍቅሬ ትኖራላችሁ። 11 ደስታዬም በእናንተ እንዲሆን ደስታችሁም እንዲፈጸም ይህን ነግሬአችኋለሁ። 12 እኔ እንደ ወደድኋችሁ እርስ በርሳችሁ ትዋደዱ ዘንድ ትእዛዜ ይህች ናት። 13 ነፍሱን ስለ ወዳጆቹ ከመስጠት ይልቅ ከዚህ የሚበልጥ ፍቅር ለማንም የለውም። 14 እኔ ያዘዝኋችሁን ሁሉ ብታደርጉ እናንተ ወዳጆቼ ናችሁ። 15 ከእንግዲህ ወዲህ ባሮች አልላችሁም፤ ባርያ ጌታው የሚያደርገውን አያውቅምና፤ ወዳጆች ግን ብያችኋለሁ፥ ከአባቴ የሰማሁትን ሁሉ ለእናንተ አስታውቄአችኋለሁና። 16 እኔ መረጥኋችሁ እንጂ እናንተ አልመረጣችሁኝም፤ አብም በስሜ የምትለምኑትን ሁሉ እንዲሰጣችሁ፥ ልትሄዱና ፍሬ ልታፈሩ ፍሬአችሁም ሊኖር ሾምኋችሁ። 17 እርስ በርሳችሁ እንድትዋደዱ ይህን አዛችኋለሁ። 18 ዓለም ቢጠላችሁ ከእናንተ በፊት እኔን እንደ ጠላኝ እወቁ። 19 ከዓለምስ ብትሆኑ ዓለም የራሱ የሆነውን ይወድ ነበር፤ ነገር ግን እኔ ከዓለም መረጥኋችሁ እንጂ ከዓለም ስለ አይደላችሁ ስለዚህ ዓለም ይጠላችኋል። 20 ባርያ ከጌታው አይበልጥም ብዬ የነገርኋችሁን ቃል አስቡ። እኔን አሳደውኝ እንደ ሆኑ እናንተን ደግሞ ያሳድዱአችኋል፤ ቃሌን ጠብቀው እንደ ሆኑ ቃላችሁን ደግሞ ይጠብቃሉ። 21 ዳሩ ግን የላከኝን አያውቁምና ይህን ሁሉ ሰለ ስሜ ያደርጉባችኋል። 22 እኔ መጥቼ ባልነገርኋቸውስ ኃጢአት ባልሆነባቸውም ነበር፤ አሁን ግን ለኃጢአታቸው ምክንያት የላቸውም። 23 እኔን የሚጠላ አባቴን ደግሞ ይጠላል። 24 ሌላ ሰው ያላደረገውን ሥራ በመካከላቸው ባላደረግሁ፥ ኃጢአት ባልሆነባቸውም ነበር፤ አሁን ግን እኔንም አባቴንም አይተውማል ጠልተውማል። 25 ነገር ግን በሕጋቸው። በከንቱ ጠሉኝ ተብሎ የተጻፈው ቃል ይፈጸም ዘንድ ነው። 26 ዳሩ ግን እኔ ከአብ ዘንድ የምልክላችሁ አጽናኝ እርሱም ከአብ የሚወጣ የእውነት መንፈስ በመጣ ጊዜ፥ እርሱ ስለ እኔ ይመሰክራል፤ 27 እናንተም ደግሞ ከመጀመሪያ ከእኔ ጋር ኖራችኋልና ትመሰክራላችሁ።16 1 እንዳትሰናከሉ ይህን ተናግሬአችኋለሁ። 2 ከምኵራባቸው ያወጡአችኋል፤ ከዚህ በላይ ደግሞ የሚገድላችሁ ሁሉ እግዚአብሔርን እንደሚያገለግል የሚመስልበት ጊዜ ይመጣል። 3 ይህንም የሚያደርጉባችሁ አብንና እኔን ስላላወቁ ነው። 4 ነገር ግን ጊዜው ሲደርስ እኔ እንደ ነገርኋችሁ ታስቡ ዘንድ ይህን ተናግሬአችኋለሁ። ከእንናንተም ጋር ስለ ነበርሁ በመጀመሪያ ይህን አልነገርኋችሁም። 5 አሁን ግን ወደ ላከኝ እሄዳለሁ ከእናንተም። ወዴት ትሄዳለህ? ብሎ የሚጠይቀኝ የለም። 6 ነገር ግን ይህን ስለ ተናገርኋችሁ ኀዘን በልባችሁ ሞልቶአል። 7 እኔ ግን እውነት እነግራችኋለሁ፤ እኔ እንድሄድ ይሻላችኋል። እኔ ባልሄድ አጽናኙ ወደ እናንተ አይመጣምና፤ እኔ ብሄድ ግን እርሱን እልክላችኋለሁ። 8 እርሱም መጥቶ ስለ ኃጢአት ስለ ጽድቅም ስለ ፍርድም ዓለምን ይወቅሳል፤ 9 ስለ ኃጢአት፥ በእኔ ስለማያምኑ ነው፤ ስለ ጽድቅም፥ ወደ አብ ስለምሄድ ከዚህም በኋላ ስለማታዩኝ ነው፤ 11 ስለ ፍርድም፥ የዚህ ዓለም ገዥ ስለ ተፈረደበት ነው። 12 የምነግራችሁ ገና ብዙ አለኝ፥ ነገር ግን አሁን ልትሸከሙት አትችሉም። 13 ግን እርሱ የእውነት መንፈስ በመጣ ጊዜ ወደ እውነት ሁሉ ይመራችኋል፤ የሚሰማውን ሁሉ ይናገራል እንጂ ከራሱ አይነግርምና፤ የሚመጣውንም ይነግራችኋል። 14 እርሱ ያከብረኛል፥ ለእኔ ካለኝ ወስዶ ይነግራችኋልና። 15 ለአብ ያለው ሁሉ የእኔ ነው፤ ስለዚህ። ለእኔ ካለኝ ወስዶ ይነግራችኋል አልሁ። 16 ጥቂት ጊዜ አለ፥ አታዩኝምም፤ ደግሞም ጥቂት ጊዜ አለ፥ ታዩኛላችሁም፥ እኔ ወደ አብ እሄዳለሁና። 17 ከደቀ መዛሙርቱም አንዳንዶቹ እርስ በርሳቸው። ጥቂት ጊዜ አለ፥ አታዩኝምም፤ ደግሞም ጥቂት ጊዜ አለ፥ ታዩኛላችሁም፤ ደግሞ። ወደ አብ እሄዳለሁና የሚለን ይህ ምንድር ነው? ተባባሉ። 18 እንግዲህ። ጥቂት የሚለው ይህ ምንድር ነው? የሚናገረውን አናውቅም አሉ። 19 ኢየሱስም ሊጠይቁት እንደ ወደዱ አውቆ እንዲህ አላቸው። ጥቂት ጊዜ አለ፥ አታዩኝምም፤ ደግሞም ጥቂት ጊዜ አለ፥ ታዩኛላችሁ ስላልሁ፥ ስለዚህ እርስ በርሳችሁ ትመራመራላችሁን? 20 እውነት እውነት እላችኋለሁ፥ እናንተ ታለቅሳለችሁ ሙሾም ታወጣላችሁ፥ ዓለም ግን ደስ ይለዋል፤ እናንተም ታዝናላችሁ፥ ነገር ግን ኀዘናችሁ ወደ ደስታ ይለወጣል። 21 ሴት በምትወልድበት ጊዜ ወራትዋ ስለ ደረሰ ታዝናለች፤ ነገር ግን ሕፃን ከወለደች በኋላ፥ ሰው በዓለም ተወልዶአልና ስለ ደስታዋ መከራዋን ኋላ አታስበውም። 22 እንግዲህ እናንተ ደግሞ አሁን ታዝናላችሁ፤ ነገር ግን እንደ ገና አያችኋለሁ ልባችሁም ደስ ይለዋል፥ ደስታችሁንም የሚወስድባችሁ የለም። 23 በዚያን ቀንም ከእኔ አንዳች አትለምኑም። እውነት እውነት እላችኋለሁ፥ አብ በስሜ የምትለምኑትን ሁሉ ይሰጣችኋል። 24 እስከ አሁን በስሜ ምንም አልለመናችሁም፤ ደስታችሁ ፍጹም እንዲሆን ለምኑ ትቀበሉማላችሁ። 25 ይህን በምሳሌ ነግሬአችኋለሁ፤ ነገር ግን ስለ አብ ለእናንተ በግልጥ የምናገርበት እንጂ ከዚያ ወዲያ በምሳሌ የማልናገርበት ሰዓት ይመጣል። 26 በዚያን ቀን በስሜ ትለምናላችሁ፤ እኔም ስለ እናንተ አብን እንድለምን የምላችሁ አይደለሁም፤ 27 እናንተ ስለ ወደዳችሁኝ ከእግዚአብሔርም ዘንድ እኔ እንደ ወጣሁ ስላመናችሁ አብ እርሱ ራሱ ይወዳችኋልና። 28 ከአብ ወጥቼ ወደ ዓለም መጥቻለሁ፤ ደግሞ ዓለምን እተወዋለሁ ወደ አብም እሄዳለሁ። 29 ደቀ መዛሙርቱ። እነሆ፥ አሁን በግልጥ ትናገራለህ በምሳሌም ምንም አትነግርም። 30 ሁሉን እንድታውቅ ማንምም ሊጠይቅህ እንዳትፈልግ አሁን እናውቃለን፤ ስለዚህ ከእግዚአብሔር እንደ ወጣህ እናምናለን አሉት። 31 ኢየሱስም እንዲህ ብሎ መለሰላቸው። አሁን ታምናላችሁን? 32 እነሆ፥ እያንዳንዳችሁ ወደ ቤት የምትበታተኑበት እኔንም ለብቻዬ የምትተዉበት ሰዓት ይመጣል፥ አሁንም ደርሶአል፤ ነገር ግን አብ ከእኔ ጋር ስለ ሆነ ብቻዬን አይደለሁም። 33 በእኔ ሳላችሁ ሰላም እንዲሆንላችሁ ይህን ተናግሬአችኋለሁ። በዓለም ሳላችሁ መከራ አለባችሁ፤ ነገር ግን አይዞአችሁ፤ እኔ ዓለምን አሸንፌዋለሁ።