Amharic(i)
40 ሕፃኑም አደገ፥ ጥበብም ሞልቶበት በመንፈስ ጠነከረ፤ የእግዚአብሔርም ጸጋ በእርሱ ላይ ነበረ። 41 ወላጆቹም በያመቱ በፋሲካ በዓል ወደ ኢየሩሳሌም ይወጡ ነበር። 42 የአሥራ ሁለት ዓመት ልጅ በሆነ ጊዜ፥ እንደ በዓሉ ሥርዓት ወደ ኢየሩሳሌም ወጡ፤ 43 ቀኖቹንም ከፈጸሙ በኋላ፥ ሲመለሱ ብላቴናው ኢየሱስ በኢየሩሳሌም ቀርቶ ነበር፥ ዮሴፍም እናቱም አላወቁም ነበር። 44 ከመንገደኞች ጋር የነበረ ስለ መሰላቸው የአንድ ቀን መንገድ ሄዱ፥ ከዘመዶቻቸውም ከሚያውቋቸውም ዘንድ ፈለጉት፤ 45 ባጡትም ጊዜ እየፈለጉት ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሱ። 46 ከሦስት ቀንም በኋላ በመምህራን መካከል ተቀምጦ ሲሰማቸውም ሲጠይቃቸውም በመቅደስ አገኙት፤ 47 የሰሙትም ሁሉ በማስተዋሉና በመልሱ ተገረሙ። 48 ባዩትም ጊዜ ተገረሙ፥ እናቱም። ልጄ ሆይ፥ ለምን እንዲህ አደረግህብን? እነሆ፥ አባትህና እኔ እየተጨነቅን ስንፈልግህ ነበርን አለችው። 49 እርሱም። ስለ ምን ፈለጋችሁኝ? በአባቴ ቤት እሆን ዘንድ እንዲገባኝ አላወቃችሁምን? አላቸው። 50 እነርሱም የተናገራቸውን ነገር አላስተዋሉም። 51 ከእነርሱም ጋር ወርዶ ወደ ናዝሬት መጣ፥ ይታዘዝላቸውም ነበር። እናቱም ይህን ነገር ሁሉ በልብዋ ትጠብቀው ነበር። 52 ኢየሱስም ደግሞ በጥበብና በቁመት በሞገስም በእግዚአብሔርና በሰው ፊት ያድግ ነበር።