Amharic(i)
27 ከዚህም በኋላ ወጥቶ ሌዊ የሚባል ቀራጭ በመቅረጫው ተቀምጦ ተመለከተና። ተከተለኝ አለው። 28 ሁሉንም ተወ፤ ተነሥቶም ተከተለው። 29 ሌዊም በቤቱ ታላቅ ግብዣ አደረገለት፤ ከእነርሱም ጋር በማዕድ ተቀምጠው የነበሩ ከቀራጮችና ከሌሎች ሰዎች ብዙ ሕዝብ ነበሩ። 30 ፈሪሳውያንና ጻፎቻቸውም በደቀ መዛሙርቱ ላይ። ስለ ምን ከቀራጮችና ከኃጢአተኞች ጋር ትበላላችሁ ትጠጡማላችሁ? ብለው አንጐራጐሩ። 31 ኢየሱስም መልሶ። ሕመምተኞች እንጂ ባለ ጤናዎች ባለ መድኃኒት አያስፈልጋቸውም፤ 32 ኃጢአተኞችን ወደ ንስሐ እንጂ ጻድቃንን ልጠራ አልመጣሁም አላቸው። 33 እነርሱም። የዮሐንስ ደቀ መዛሙርት ስለ ምን ብዙ ይጦማሉ ጸሎትስ ስለ ምን ያደርጋሉ፥ ደግሞም የፈሪሳውያን ደቀ መዛሙርት ስለ ምን እንደዚሁ ያደርጋሉ፤ የአንተ ደቀ መዛሙርት ግን ይበላሉ ይጠጣሉም? አሉት። 34 ኢየሱስም። ሙሽራው ከእነርሱ ጋር ሳለ ሚዜዎችን ልታስጦሙ ትችላላችሁን? 35 ነገር ግን ወራት ይመጣል፥ ሙሽራውም ከእነርሱ ሲወሰድ ያንጊዜ፥ በዚያ ወራት ይጦማሉ አላቸው። 36 ደግሞም ምሳሌ እንዲህ ሲል ነገራቸው። የአዲስ ልብስ እራፊ ባረጀ ልብስ ላይ የሚያኖር የለም፤ ቢደረግ ግን አዲሱን ይቀደዋል ደግሞም አዲስ እራፊ ለአሮጌው አይስማማውም። 37 ባረጀ አቁማዳም አዲስ የወይን ጠጅ የሚያኖር የለም፤ ቢደረግ ግን አዲሱ የወይን ጠጅ አቁማዳውን ያፈነዳል፥ እርሱም ይፈሳል አቁማዳውም ይጠፋል። 38 አዲሱን የወይን ጠጅ ግን በአዲስ አቁማዳ ማኖር ይገባል፥ ሁለቱም ይጠባበቃሉ።