Amharic(i)
7 መልአኩም አለኝ። የምትደነቅ ስለ ምንድር ነው? የሴቲቱን ምስጢርና የሚሸከማትን፥ ሰባት ራሶችና አስር ቀንዶች ያሉትን የአውሬውን ምስጢር እኔ እነግርሃለሁ። 8 ያየኸው አውሬ አስቀድሞ ነበረ፥ አሁንም የለም፥ ከጥልቁም ይወጣ ዘንድ አለው፥ ወደ ጥፋትም ይሄዳል፤ ስሞቻቸውም ከዓለም ፍጥረት ጀምሮ በሕይወት መጽሐፍ ያልተጻፉ በምድር የሚኖሩ አውሬው አስቀድሞ እንደነበረ አሁንም እንደሌለ፥ ነገር ግን እንዳለ ሲያዩ ያደንቃሉ። 9 ጥበብ ያለው አእምሮ በዚህ ነው። ሰባቱ ራሶች ሴቲቱ የተቀመጠችባቸው ሰባት ተራራዎች ናቸው፥ 10 ሰባት ነገሥታት ደግሞ ናቸው፤ አምስቱ ወድቀዋል አንዱም አለ፥ የቀረውም ገና አልመጣም፤ ሲመጣም፥ ጥቂት ጊዜ ሊቆይ ይገባዋል። 11 የነበረውና የሌለውም አውሬ ራሱ ደግሞ ስምንተኛው ነው ከሰባቱም አንዱ ነው፥ ወደ ጥፋትም ይሄዳል። 12 ያየሃቸውም አስሩ ቀንዶች ገና መንግሥትን ያልተቀበሉ አስር ነገሥታት ናቸው፥ ዳሩ ግን ከአውሬው ጋር ለአንድ ሰዓት እንደ ነገሥታት ሥልጣንን ይቀበላሉ።