Acts 4:8-22

Amharic(i) 8 በዚያን ጊዜ ጴጥሮስ መንፈስ ቅዱስንም ተሞልቶ እንዲህ አላቸው። እናንተ የሕዝብ አለቆችና ሽማግሌዎች፥ 9 እኛ ዛሬ ለድውዩ ሰው ስለ ተደረገው መልካም ሥራ ይህ በምን እንደዳነ ብንመረመር፥ 10 እናንተ በሰቀላችሁት እግዚአብሔርም ከሙታን ባስነሣው በናዝሬቱ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ይህ ደኅና ሆኖ በፊታችሁ እንደ ቆመ፥ ለእናንተ ለሁላችሁ ለእስራኤልም ሕዝብ ሁሉ የታወቀ ይሁን። 11 እናንተ ግንበኞች የናቃችሁት፥ የማዕዘን ራስ የሆነው ይህ ድንጋይ ነው። 12 መዳንም በሌላ በማንም የለም፤ እንድንበት ዘንድ የሚገባን ለሰዎች የተሰጠ ስም ከሰማይ በታች ሌላ የለምና። 13 ጴጥሮስና ዮሐንስም በግልጥ እንደ ተናገሩ ባዩ ጊዜ፥ መጽሐፍን የማያውቁና ያልተማሩ ሰዎች እንደ ሆኑ አስተውለው አደነቁ፥ ከኢየሱስም ጋር እንደ ነበሩ አወቁአቸው፤ 14 የተፈወሰውንም ሰው ከእነርሱ ጋር ቆሞ ሲያዩ የሚመልሱትን አጡ። 15 ከሸንጎም ወደ ውጭ ይወጡ ዘንድ አዝዘው። በእነዚህ ሰዎች ምን እንሥራ? 16 የታወቀ ምልክት በእነርሱ እጅ እንደ ተደረገ በኢየሩሳሌም ለሚኖሩ ሁሉ ተገልጦአልና፥ እንሸሽገው ዘንድ አንችልም፤ 17 ነገር ግን በሕዝቡ ዘንድ አብዝቶ እንዳይስፋፋ፥ ከእንግዲህ ወዲህ ለማንም ሰው በዚህ ስም እንዳይናገሩ እየዛትን እንዘዛቸው ብለው እርስ በርሳቸው ተማከሩ። 18 ጠርተውም በኢየሱስ ስም ፈጽመው እንዳይናገሩና እንዳያስተምሩ አዘዙአቸው። 19 ጴጥሮስና ዮሐንስ ግን መልሰው። እግዚአብሔርን ከመስማት ይልቅ እናንተን እንሰማ ዘንድ በእግዚአብሔር ፊት የሚገባ እንደ ሆነ ቍረጡ፤ 20 እኛስ ያየነውንና የሰማነውን ከመናገር ዝም ማለት አንችልም አሉአቸው። 21 እነርሱም እንደ ምን እንደሚቀጡ ምክንያት ስላላገኙባቸው፥ እንደ ገና ዝተው ከሕዝቡ የተነሣ ፈቱአቸው፤ ሰዎች ሁሉ ስለ ሆነው ነገር እግዚአብሔርን ያከብሩ ነበርና። 22 ይህ የመፈወስ ምልክት የተደረገለት ሰው ከአርባ ዓመት ይበልጠው ነበርና።