Amharic(i)
1 በሰንበትም መጨረሻ መጀመሪያው ቀን ሲነጋ መግደላዊት ማርያምና ሁለተኛይቱ ማርያም መቃብሩን ሊያዩ መጡ። 2 እነሆም፥ የጌታ መልአክ ከሰማይ ስለ ወረደ ታላቅ የምድር መናወጥ ሆነ፤ ቀርቦም ድንጋዩን አንከባሎ በላዩ ተቀመጠ። 3 መልኩም እንደ መብረቅ ልብሱም እንደ በረዶ ነጭ ነበረ። 4 ጠባቆቹም እርሱን ከመፍራት የተነሣ ተናወጡ እንደ ሞቱም ሆኑ። 5 መልአኩም መልሶ ሴቶቹን አላቸው። እናንተስ አትፍሩ የተሰቀለውን ኢየሱስን እንድትሹ አውቃለሁና፤ 6 እንደ ተናገረ ተነሥቶአልና በዚህ የለም፤ የተኛበትን ስፍራ ኑና እዩ። 7 ፈጥናችሁም ሂዱና። ከሙታን ተነሣ፥ እነሆም፥ ወደ ገሊላ ይቀድማችኋል በዚያም ታዩታላችሁ ብላችሁ ለደቀ መዛሙርቱ ንገሩአቸው። 8 እነሆም፥ ነገርኋችሁ። በፍርሃትና በታላቅ ደስታም ፈጥነው ከመቃብር ሄዱ፥ ለደቀ መዛሙርቱም ሊያወሩ ሮጡ። 9 እነሆም፥ ኢየሱስ አገኛቸውና። ደስ ይበላችሁ አላቸው። እነርሱም ቀርበው እግሩን ይዘው ሰገዱለት። 10 በዚያን ጊዜ ኢየሱስ። አትፍሩ፤ ሄዳችሁ ወደ ገሊላ እንዲሄዱ ለወንድሞቼ ተናገሩ፥ በዚያም ያዩኛል አላቸው።