Amharic(i)
18 በነገውም ጳውሎስ ከእኛ ጋር ወደ ያዕቆብ ዘንድ ገባ ሽማግሌዎችም ሁሉ መጡ። 19 ሰላምታም ካቀረበላቸው በኋላ በእርሱ ማገልገል እግዚአብሔር በአሕዛብ መካከል ያደረገውን በእያንዳንዱ ተረከላቸው። 20 እነርሱም በሰሙ ጊዜ እግዚአብሔርን አመሰገኑ አሉትም። ወንድም ሆይ፥ በአይሁድ መካከል አምነው የነበሩት ስንት አእላፋት እንደ ሆኑ ታያለህ፤ ሁላቸውም ለሕግ የሚቀኑ ናቸው። 21 ልጆቻቸውንም እንዳይገርዙ በሥርዓትም እንዳይሄዱ ብለህ በአሕዛብ መካከል ያሉት አይሁድ ሁሉ ሙሴን ይክዱ ዘንድ እንድታስተምር ስለ አንተ ነግረዋቸዋል። 22 እንግዲህ ምን ይሁን? የአንተን መምጣት ይሰማሉና ብዙዎች የግድ ሳይሰበሰቡ አይቀሩም። 23 እንግዲህ ይህን የምንልህን አድርግ፤ ስለት ያለባቸው አራት ሰዎች በእኛ ዘንድ አሉ። 24 እነዚህንም ይዘህ ከእነርሱ ጋር ንጻ፥ ራሳቸውንም እንዲላጩ ገንዘብ ክፈልላቸው፤ ሁሉም ስለ አንተ የተማሩት ከንቱ እንደ ሆነና አንተ ራስህ ደግሞ ሕጉን እየጠበቅህ በሥርዓት እንድትመላለስ ያውቃሉ። 25 አምነው ስለ ነበሩ አሕዛብ ግን ለጣዖት ከተሠዋ ከደምም ከታነቀም ከዝሙትም ነፍሳቸውን እንዲጠብቁ ፈርደን እኛ ጽፈንላቸዋል።