2 John 1

Amharic(i) 1 በእኛ ስለሚኖርና ከእኛ ጋር ለዘላለም ስለሚሆን እውነት፥ እኔ ሽማግሌው በእውነት ለምወዳቸውና እኔ ብቻ ሳልሆን እውነትን የሚያውቁ ሁሉ ደግሞ ለሚወዱአቸው ለተመረጠች እመቤትና ለልጆችዋ፤ 3 ከእግዚአብሔር አብና ከአብ ልጅ ከኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋና ምሕረት ሰላምም በእውነትና በፍቅር ከእኛ ጋር ይሆናሉ። 4 ትእዛዝን ከአብ እንደ ተቀበልን ከልጆችሽ በእውነት የሚሄዱ አንዳንዶችን ስለ አገኘኋቸው እጅግ ደስ ብሎኛል። 5 አሁንም፥ እመቤት ሆይ፥ እርስ በርሳችን እንድንዋደድ እለምንሻለሁ፤ ይህች ከመጀመሪያ በእኛ ዘንድ የነበረች ትእዛዝ ናት እንጂ አዲስ ትእዛዝን እንደምጽፍልሽ አይደለም። 6 እንደ ትእዛዛቱም እንሄድ ዘንድ ይህ ፍቅር ነው፤ ከመጀመሪያ እንደ ሰማችሁ፥ በእርስዋ ትሄዱ ዘንድ ትእዛዙ ይህች ናት። 7 ብዙ አሳቾች ወደ ዓለም ገብተዋልና እነርሱም ኢየሱስ ክርስቶስ በሥጋ እንደ መጣ የማያምኑ ናቸው፤ ይህ አሳቹና የክርስቶስ ተቃዋሚው ነው። 8 ሙሉ ደመወዝን እንድትቀበሉ እንጂ የሠራችሁትን እንዳታጠፉ ለራሳችሁ ተጠንቀቁ። 9 ለሚወጣ ሁሉ በክርስቶስም ትምህርት ለማይኖር ሰው አምላክ የለውም፤ በክርስቶስ ትምህርት ለሚኖር አብና ወልድ አሉት። 10 ማንም ወደ እናንተ ቢመጣ ይህንም ትምህርት ባያመጣ በቤታችሁ አትቀበሉት ሰላምም አትበሉት፤ 11 ሰላም የሚለው ሰው በክፉ ሥራው ይካፈላልና። 12 እንድጽፍላችሁ የምፈልገው ብዙ ነገር ሳለኝ በወረቀትና በቀለም ልጽፈው አልወድም፥ ዳሩ ግን ደስታችሁ ፍጹም እንዲሆን ወደ እናንተ ልመጣ አፍ ለአፍም ልናገራችሁ ተስፋ አደርጋለሁ። 13 የተመረጠችው የእኅትሽ ልጆች ሰላምታ ያቀርቡልሻል።