Amharic(i)
16 እርሱ ስለ እኛ ነፍሱን አሳልፎ ሰጥቶአልና በዚህ ፍቅርን አውቀናል፤ እኛም ስለ ወንድሞቻችን ነፍሳችንን አሳልፈን እንድንሰጥ ይገባናል። 17 ነገር ግን የዚህ ዓለም ገንዘብ ያለው፥ ወንድሙም የሚያስፈልገው ሲያጣ አይቶ ያልራራለት ማንም ቢሆን፥ የእግዚአብሔር ፍቅር በእርሱ እንዴት ይኖራል? 18 ልጆቼ ሆይ፥ በሥራና በእውነት እንጂ በቃልና በአንደበት አንዋደድ። 19 ልባችንም በእኛ ላይ በሚፈርድበት ሁሉ፥ ከእውነት እንደ ሆንን በዚህ እናውቃለን በፊቱም ልባችንን እናሳርፋለን፥ እግዚአብሔር ከልባችን ይልቅ ታላቅ ነውና ሁሉንም ያውቃል። 21 ወዳጆች ሆይ፥ ልባችንስ ባይፈርድብን በእግዚአብሔር ዘንድ ድፍረት አለን፥ 22 ትእዛዙንም የምንጠብቅና በፊቱ ደስ የሚያሰኘውን የምናደርግ ስለሆንን የምንለምነውን ሁሉ ከእርሱ እናገኛለን። 23 ትእዛዚቱም ይህች ናት፥ በልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም እናምን ዘንድ፥ ትእዛዝንም እንደ ሰጠን እርስ በርሳችን እንዋደድ ዘንድ። 24 ትእዛዙንም የሚጠብቅ በእርሱ ይኖራል እርሱም ይኖርበታል፤ በዚህም በእኛ እንዲኖር ከሰጠን ከመንፈሱ እናውቃለን።