1 Corinthians 15:3-11

Amharic(i) 3 እኔ ደግሞ የተቀበልሁትን ከሁሉ በፊት አሳልፌ ሰጠኋችሁ እንዲህ ብዬ። መጽሐፍ እንደሚል ክርስቶስ ስለ ኃጢአታችን ሞተ፥ ተቀበረም፥ 4 መጽሐፍም እንደሚል በሦስተኛው ቀን ተነሣ፥ 5 ለኬፋም ታየ በኋላም ለአሥራ ሁለቱ፤ 6 ከዚያም በኋላ ከአምስት መቶ ለሚበዙ ወንድሞች በአንድ ጊዜ ታየ፤ ከእነርሱም የሚበዙቱ እስከ አሁን አሉ አንዳንዶች ግን አንቀላፍተዋል፤ 7 ከዚያም በኋላ ለያዕቆብ ኋላም ለሐዋርያት ሁሉ ታየ፤ 8 ከሁሉም በኋላ እንደ ጭንጋፍ ለምሆን ለእኔ ደግሞ ታየኝ። 9 እኔ ከሐዋርያት ሁሉ የማንስ ነኝና፥ የእግዚአብሔርን ቤተ ክርስቲያን ስላሳደድሁ ሐዋርያ ተብዬ ልጠራ የማይገባኝ፤ 10 ነገር ግን በእግዚአብሔር ጸጋ የሆንሁ እኔ ነኝ፤ ለእኔም የተሰጠኝ ጸጋው ከንቱ አልነበረም ከሁላቸው ይልቅ ግን ደከምሁ፥ ዳሩ ግን ከእኔ ጋር ያለው የእግዚአብሔር ጸጋ ነው እንጂ እኔ አይደለሁም። 11 እንግዲህስ እኔ ብሆን እነርሱም ቢሆኑ እንዲሁ እንሰብካለን እንዲሁም አመናችሁ።