Amharic(i)
10 ደግሞም። አሕዛብ ሆይ፥ ከሕዝቡ ጋር ደስ ይበላችሁ ይላል። 11 ደግሞም። እናንተ አሕዛብ ሁላችሁ፥ ጌታን አመስግኑ ሕዝቦቹም ሁሉ ይወድሱት ይላል። 12 ደግሞም ኢሳይያስ። የእሴይ ሥር አሕዛብንም ሊገዛ የሚነሣው ይሆናል፤ በእርሱ አሕዛብ ተስፋ ያደርጋሉ ይላል። 13 የተስፋ አምላክም በመንፈስ ቅዱስ ኃይል በተስፋ እንድትበዙ በማመናችሁ ደስታንና ሰላምን ሁሉ ይሙላባችሁ። 14 እኔም ራሴ ደግሞ፥ ወንድሞቼ ሆይ፥ በበጎነት ራሳችሁ እንደ ተሞላችሁ፥ እውቀትም ሁሉ እንደ ሞላባችሁ፥ እርስ በርሳችሁም ደግሞ ልትገሠጹ እንዲቻላችሁ ስለ እናንተ ተረድቼአለሁ። 15 ነገር ግን አሕዛብ በመንፈስ ቅዱስ ተቀድሰው የተወደደ መሥዋዕት ሊሆኑ፥ ለእግዚአብሔር ወንጌል እንደ ካህን እያገለገልሁ፥ ለአሕዛብ የክርስቶስ ኢየሱስ አገልጋይ እሆን ዘንድ ከእግዚአብሔር በተሰጠኝ ጸጋ ምክንያት ተመልሼ ላሳስባችሁ ብዬ በአንዳንድ ቦታ በድፍረት ጻፍሁላችሁ። 17 እንግዲህ ከእግዚአብሔር ዘንድ በሚሆን ነገር በክርስቶስ ኢየሱስ ትምክህት አለኝ። 18 አሕዛብ እንዲታዘዙ ክርስቶስ በቃልና በሥራ፥ በምልክትና በድንቅ ነገር ኃይል፥ በመንፈስ ቅዱስም ኃይል በእኔ አድርጎ ከሠራው በቀር ምንም ልናገር አልደፍርም፤ ስለዚህ ከኢየሩሳሌም ጀምሬ እስከ እልዋሪቆን ድረስ እየዞርሁ የክርስቶስን ወንጌል ፈጽሜ፤ ሰብኬአለሁ።