Revelation 7:10-17

Amharic(i) 10 በታላቅም ድምፅ እየጮሁ። በዙፋኑ ላይ ለተቀመጠው ለአምላካችንና ለበጉ ማዳን ነው አሉ። 11 መላእክቱም ሁሉ በዙፋኑና በሽማግሌዎቹ በአራቱም እንስሶቹ ዙሪያ ቆመው ነበር፤ በዙፋኑም ፊት በግምባራቸው ተደፉ፥ ለእግዚአብሔርም እየሰገዱ። 12 አሜን፥ በረከትና ክብር ጥበብም ምስጋናም ውዳሴም ኃይልም ብርታትም ከዘላለም እስከ ዘላለም ድረስ ለአምላካችን ይሁን፤ አሜን አሉ። 13 ከሽማግሌዎቹም አንዱ ተመልሶ። እነዚህ ነጩን ልብስ የለበሱ እነማን ናቸው? ከወዴትስ መጡ? አለኝ። 14 እኔም። ጌታ ሆይ፥ አንተ ታውቃለህ አልሁት። አለኝም። እነዚህ ከታላቁ መከራ የመጡ ናቸው፥ ልብሳቸውንም አጥበው በበጉ ደም አነጹ። 15 ስለዚህ በእግዚአብሔር ዙፋን ፊት አሉ፥ ሌሊትና ቀንም በመቅደሱ ያመልኩታል፥ በዙፋኑም ላይ የተቀመጠው በእነርሱ ላይ ያድርባቸዋል። 16 ከእንግዲህ ወዲህ አይራቡም፥ ከእንግዲህም ወዲህ አይጠሙም፥ ፀሐይም ትኵሳትም ሁሉ ከቶ አይወርድባቸውም፤ 17 በዙፋኑ መካከል ያለው በጉ እረኛቸው ይሆናልና፥ ወደ ሕይወትም ውኃ ምንጭ ይመራቸዋልና፤ እግዚአብሔርም እንባዎችን ሁሉ ከዓይናቸው ያብሳል።