Amharic(i)
5 ድል የነሣው እንዲሁ በነጭ ልብስ ይጐናጸፋል፥ ስሙንም ከሕይወት መጽሐፍ አልደመስስም፥ በአባቴና በመላእክቱም ፊት ለስሙ እመሰክርለታለሁ። 6 መንፈስ ለአብያተ ክርስቲያናት የሚለውን ጆሮ ያለው ይስማ። 7 በፊልድልፍያም ወዳለው ወደ ቤተ ክርስቲያን መልአክ እንዲህ ብለህ ጻፍ። የዳዊት መክፈቻ ያለው፤ የሚከፍት፥ የሚዘጋም የሌለ፤ የሚዘጋ፥ የሚከፍትም የሌለ፤ ቅዱስና እውነተኛ የሆነው እርሱ እንዲህ ይላል። 8 ሥራህን አውቃለሁ፤ እነሆ፥ በአንተ ፊት የተከፈተ በር ሰጥቼአለሁ ማንምም ሊዘጋው አይችልም፤ ኃይልህ ምንም ትንሽ ቢሆን ቃሌን ጠብቀሃልና፥ ስሜንም አልካድህምና። 9 እነሆ፥ አይሁድ ሳይሆኑ። አይሁድ ነን ከሚሉ ነገር ግን ከሚዋሹ ከሰይጣን ማኅበር አንዳንዶችን እሰጥሃለሁ እነሆ፥ መጥተው በእግሮችህ ፊት ይሰግዱ ዘንድ እኔም እንደ ወደድሁህ ያውቁ ዘንድ አደርጋቸዋለሁ። 10 የትዕግሥቴን ቃል ስለ ጠበቅህ እኔ ደግሞ በምድር የሚኖሩትን ይፈትናቸው ዘንድ በዓለም ሁሉ ላይ ሊመጣ ካለው ከፈተናው ሰዓት እጠብቅሃለሁ። 11 እነሆ፥ ቶሎ ብዬ እመጣለሁ፤ ማንም አክሊልህን እንዳይወስድብህ ያለህን አጽንተህ ያዝ። 12 ድል የነሣው በአምላኬ መቅደስ ዓምድ እንዲሆን አደርገዋለሁ፥ ወደ ፊትም ከዚያ ከቶ አይወጣም፤ የአምላኬን ስምና የአምላኬን ከተማ ስም፥ ማለት ከሰማይ ከአምላኬ ዘንድ የምትወርደውን አዲሲቱን ኢየሩሳሌምን፥ አዲሱንም ስሜን በእርሱ ላይ እጽፋለሁ። 13 መንፈስ ለአብያተ ክርስቲያናት የሚለውን ጆሮ ያለው ይስማ። 14 በሎዶቅያም ወዳለው ወደ ቤተ ክርስቲያን መልአክ እንዲህ ብለህ ጻፍ። አሜን የሆነው፥ የታመነውና እውነተኛው ምስክር፥ በእግዚአብሔርም ፍጥረት መጀመሪያ የነበረው እንዲህ ይላል። 15 በራድ ወይም ትኩስ እንዳይደለህ ሥራህን አውቃለሁ። በራድ ወይም ትኩስ ብትሆንስ መልካም በሆነ ነበር። 16 እንዲሁ ለብ ስላልህ በራድም ወይም ትኩስ ስላልሆንህ ከአፌ ልተፋህ ነው። 17 ሀብታም ነኝና ባለጠጋ ሆኜአለሁ አንድም ስንኳ አያስፈልገኝም የምትል ስለ ሆንህ፥ ጐስቋላና ምስኪንም ድሀም ዕውርም የተራቆትህም መሆንህን ስለማታውቅ፥ 18 ባለ ጠጋ እንድትሆን በእሳት የነጠረውን ወርቅ፥ ተጐናጽፈህም የራቁትነትህ ኃፍረት እንዳይገለጥ ነጭ ልብስን፥ እንድታይም ዓይኖችህን የምትኳለውን ኵል ከእኔ ትገዛ ዘንድ እመክርሃለሁ። 19 እኔ የምወዳቸውን ሁሉ እገሥጻቸዋለሁ እቀጣቸውማለሁ፤ እንግዲህ ቅና ንስሐም ግባ። 20 እነሆ በደጅ ቆሜ አንኳኳለሁ፤ ማንም ድምፄን ቢሰማ ደጁንም ቢከፍትልኝ፥ ወደ እርሱ እገባለሁ ከእርሱም ጋር እራት እበላለሁ እርሱም ከእኔ ጋር ይበላል። 21 እኔ ደግሞ ድል እንደ ነሣሁ ከአባቴም ጋር በዙፋኑ ላይ እንደተቀመጥሁ፥ ድል ለነሣው ከእኔ ጋር በዙፋኔ ላይ ይቀመጥ ዘንድ እሰጠዋለሁ። 22 መንፈስ ለአብያተ ክርስቲያናት የሚለውን ጆሮ ያለው ይስማ።4 1 ከዚያ በኋላም አየሁ፥ እነሆም በሰማይ የተከፈተ ደጅ፥ እንደ መለከትም ሆኖ ሲናገረኝ የሰማሁት ፊተኛው ድምፅ። ወደዚህ ውጣና ከዚህ በኋላ ሊሆን የሚያስፈልገውን ነገር አሳይሃለሁ አለ። 2 ወዲያው በመንፈስ ነበርሁ፤ እነሆም፥ ዙፋን በሰማይ ቆሞአል በዙፋኑም ላይ ተቀማጭ ነበረ፤ 3 ተቀምጦም የነበረው በመልኩ የኢያስጲድንና የሰርዲኖን ዕንቍ ይመስል ነበር። በመልኩም መረግድን የመሰለ ቀስተ ደመና በዙፋኑ ዙሪያ ነበረ። 4 በዙፋኑ ዙሪያም ሀያ አራት ዙፋኖች ነበሩ፥ በዙፋኖቹም ላይ ነጭ ልብስ ለብሰው በራሳቸውም የወርቅ አክሊል ደፍተው ሀያ አራት ሽማግሌዎች ተቀምጠው ነበር። 5 ከዙፋኑም መብረቅና ድምፅ ነጐድጓድም ይወጣል፤ በዙፋኑም ፊት ሰባት የእሳት መብራቶች ይበሩ ነበር፥ እነርሱም ሰባቱ የእግዚአብሔር መናፍስት ናቸው። 6 በዙፋኑም ፊት ብርሌ የሚመስል የብርጭቆ ባሕር ነበረ። በዙፋኑም መካከል በዙፋኑም ዙሪያ፥ በፊትና በኋላ ዓይኖች የሞሉአቸው አራት እንስሶች ነበሩ። 7 ፊተኛውም እንስሳ አንበሳን ይመስላል፥ ሁለተኛውም እንስሳ ጥጃን ይመስላል፥ ሦስተኛውም እንስሳ እንደ ሰው ፊት ነበረው፥ አራተኛውም እንስሳ የሚበረውን ንስር ይመስላል። 8 አራቱም እንስሶች እያንዳንዳቸው ስድስት ክንፎች አሉአቸው፥ በዙሪያቸውና በውስጣቸውም ዓይኖች ሞልተውባቸዋል፤ ቅዱስ፥ ቅዱስ፥ ቅዱስ፥ የነበረውና ያለ የሚመጣውም ሁሉንም የሚገዛ ጌታ አምላክ እያሉ ቀንና ሌሊት አያርፉም። 9 እንስሶቹም በዙፋን ላይ ለተቀመጠው ከዘላለምም እስከ ዘላለም በሕይወት ለሚኖረው ለእርሱ ክብርና ውዳሴ ምስጋናም በሰጡት ጊዜ፥ 10 ሀያ አራቱ ሽማግሌዎች በዙፋን ላይ በተቀመጠው ፊት ወድቀው፥ ከዘላለም እስከ ዘላለም በሕይወት ለሚኖረው እየሰገዱ። ጌታችንና አምላካችን ሆይ፥ አንተ ሁሉን ፈጥረሃልና ስለ ፈቃድህም ሆነዋልና ተፈጥረውማልና ክብር ውዳሴ ኃይልም ልትቀበል ይገባሃል እያሉ በዙፋኑ ፊት አክሊላቸውን ያኖራሉ።5 1 በዙፋኑ ላይም በተቀመጠው በቀኝ እጁ ላይ በውስጥና በኋላ የተጻፈበት በሰባትም ማኅተም የተዘጋ መጽሐፍን አየሁ። 2 ብርቱም መልአክ። መጽሐፉን ይዘረጋ ዘንድ ማኅተሞቹንም ይፈታ ዘንድ የሚገባው ማን ነው? ብሎ በታላቅ ድምፅ ሲያውጅ አየሁ። 3 በሰማይም ቢሆን በምድርም ላይ ቢሆን ከምድርም በታች ቢሆን መጽሐፉን ሊዘረጋ ወይም ሊመለከተው ማንም አልተቻለውም። 4 መጽሐፉን ሊዘረጋ ወይም ሊመለከተው የሚገባው ማንም ስላልተገኘ እጅግ አለቀስሁ። 5 ከሽማግሌዎቹም አንዱ። አታልቅስ፤ እነሆ፥ ከይሁዳ ነገድ የሆነው አንበሳ እርሱም የዳዊት ሥር መጽሐፉን ይዘረጋ ዘንድ ሰባቱንም ማኅተም ይፈታ ዘንድ ድል ነሥቶአል አለኝ። 6 በዙፋኑና በአራቱ እንስሶች መካከልም በሽማግሌዎችም መካከል እንደ ታረደ በግ ቆሞ አየሁ፥ ሰባትም ቀንዶችና ሰባት ዓይኖች ነበሩት እነርሱም ወደ ምድር ሁሉ የተላኩ የእግዚአብሔር መናፍስት ናቸው። 7 መጥቶም በዙፋን ላይ ከተቀመጠ ከዚያ ከቀኝ እጁ መጽሐፉን ወሰደው። 8 መጽሐፉንም በወሰደ ጊዜ አራቱ እንስሶችና ሀያ አራቱ ሽማግሌዎች በበጉ ፊት ወደቁ፥ እያንዳንዳቸውም በገናንና የቅዱሳን ጸሎት የሆነ ዕጣን የሞላበትን የወርቅ ዕቃ ያዙ። 9 መጽሐፉን ትወስድ ዘንድ ማኅተሞቹንም ትፈታ ዘንድ ይገባሃል፥ ታርደሃልና፥ በደምህም ለእግዚአብሔር ከነገድ ሁሉ ከቋንቋም ሁሉ ከወገንም ሁሉ ከሕዝብም ሁሉ ሰዎችን ዋጅተህ ለአምላካችን መንግሥትና ካህናት ይሆኑ ዘንድ አደረግሃቸው፥ በምድርም ላይ ይነግሣሉ እያሉ አዲስን ቅኔ ይዘምራሉ። 11 አየሁም፥ በዙፋኑም በእንስሶቹም በሽማግሌዎቹም ዙሪያ የብዙ መላእክትን ድምፅ ሰማሁ፤ ቍጥራቸውም አእላፋት ጊዜ አእላፋትና ሺህ ጊዜ ሺህ ነበር፥ 12 በታላቅም ድምፅ። የታረደው በግ ኃይልና ባለ ጠግነት ጥበብም ብርታትም ክብርም ምስጋናም በረከትም ሊቀበል ይገባዋል አሉ። 13 በሰማይና በምድርም ከምድርም በታች በባሕርም ላይ ያለ ፍጥረት ሁሉ በእነርሱም ውስጥ ያለ ሁሉ። በረከትና ክብር ምስጋናም ኃይልም ከዘላለም እስከ ዘላለም በዙፋኑ ላይ ለተቀመጠው፥ ለበጉም ይሁን ሲሉ ሰማሁ። 14 አራቱም እንስሶች። አሜን አሉ፥ ሽማግሌዎቹም ወድቀው ሰገዱ።