Revelation 21:14-21

Amharic(i) 14 ለከተማይቱም ቅጥር አሥራ ሁለት መሠረቶች ነበሩአት፥ በእነርሱም ውስጥ የአሥራ ሁለቱ የበጉ ሐዋርያት ስሞች ተጽፈው ነበር። 15 የተናገረኝም ከተማይቱንና ደጆችዋን ቅጥርዋንም ይለካ ዘንድ የወርቅ ዘንግ ነበረው። 16 ከተማይቱም አራት ማዕዘን ነበራት፥ ርዝመትዋም እንደ ስፋትዋ ልክ ነበረ። ከተማይቱንም በዘንግ ለካት አሥራ ሁለትም ሺህ ምዕራፍ ሆነች፤ ርዝመትዋና ስፋትዋ ከፍታዋም ትክክል ነው። 17 ቅጥርዋንም ለካ፥ መቶ አርባ አራት ክንድ በሰው ልክ፥ እርሱም በመልአክ ልክ። 18 ቅጥርዋም ከኢያሰጲድ የተሠራ ነበረ፥ ከተማይቱም ጥሩ ብርጭቆ የሚመስል ጥሩ ወርቅ ነበረች። 19 የከተማይቱም ቅጥር መሠረት በከበረ ድንጋይ ሁሉ ተጌጦ ነበር፤ ፊተኛው መሠረት ኢያሰጲድ፥ ሁለተኛው ሰንፔር፥ ሦስተኛው ኬልቄዶን፥ አራተኛው መረግድ፥ 20 አምስተኛው ሰርዶንክስ፥ ስድስተኛው ሰርድዮን፥ ሰባተኛው ክርስቲሎቤ፥ ስምንተኛው ቢረሌ፥ ዘጠነኛው ወራውሬ፥ አሥረኛው ክርስጵራስስ፥ አሥራ አንደኛው ያክንት፥ አሥራ ሁለተኛው አሜቴስጢኖስ ነበረ። 21 አሥራ ሁለቱም ደጆች አሥራ ሁለት ዕንቆች ነበሩ፤ እየአንዳንዱ ደጅ ከአንድ ዕንቍ የተሠራ ነበረ። የከተማይቱም አደባባይ ጥሩ ብርጭቆ የሚመስል ጥሩ ወርቅ ነበረ።