Amharic(i)
16 እናንተ። ማንም በቤተ መቅደስ የሚምል ምንም የለበትም፤ ማንም በቤተ መቅደስ ወርቅ የሚምል ግን በመሐላው ይያዛል የምትሉ፥ ዕውሮች መሪዎች፥ ወዮላችሁ። 17 እናንተ ደንቆሮዎችና ዕውሮች፥ ማናቸው ይበልጣል? ወርቁ ነውን? ወይስ ወርቁን የቀደሰው ቤተ መቅደስ? 18 ደግማችሁም። ማንም በመሠዊያው የሚምል ምንም የለበትም፤ ማንም በላዩ ባለው መባ የሚምል ግን በመሐላው ይያዛል ትላላችሁ። 19 እናንተ ደንቆሮዎችና ዕውሮች፥ ማናቸው ይበልጣል? መባው ነውን? ወይስ መባውን የሚቀድሰው መሠዊያው? 20 እንግዲህ በመሠዊያው የሚምለው በእርሱና በእርሱ ላይ ባለው ሁሉ ይምላል፤ 21 በቤተ መቅደስም የሚምለው በእርሱና በእርሱ በሚኖረው ይምላል፤ 22 በሰማይም የሚምለው በእግዚአብሔር ዙፋንና በእርሱ ላይ በተቀመጠው ይምላል። 23 እናንተ ግብዞች ጻፎችና ፈሪሳውያን፥ ከአዝሙድና ከእንስላል ከከሙንም አሥራት ስለምታወጡ፥ ፍርድንና ምሕረትን ታማኝነትንም፥ በሕግ ያለውን ዋና ነገር ስለምትተዉ፥ ወዮላችሁ፤ ሌላውን ሳትተዉ ይህን ልታደርጉ ይገባችሁ ነበር። 24 እናንተ ዕውሮች መሪዎች፥ ትንኝን የምታጠሩ ግመልንም የምትውጡ። 25 እናንተ ግብዞች ጻፎችና ፈሪሳውያን፥ በውስጡ ቅሚያና ስስት ሞልቶ ሳለ የጽዋውንና የወጭቱን ውጭ ስለምታጠሩ፥ ወዮላችሁ። 26 አንተ ዕውር ፈሪሳዊ፥ ውጭው ደግሞ ጥሩ እንዲሆን አስቀድመህ የጽዋውንና የወጭቱን ውስጡን አጥራ። 27 እናንተ ግብዞች ጻፎችና ፈሪሳውያን፥ በውጭ አምረው የሚታዩ በውስጡ ግን የሙታን አጥንት ርኩሰትም ሁሉ የተሞሉ በኖራ የተለሰኑ መቃብሮችን ስለምትመስሉ፥ ወዮላችሁ። 28 እንዲሁ እናንተ ደግሞ በውጭ ለሰው እንደ ጻድቃን ትታያላችሁ፥ በውስጣችሁ ግን ግብዝነትና ዓመፀኝነት ሞልቶባችኋል።