Amharic(i)
25 ብዙም ሕዝብ ከእርሱ ጋር ይሄዱ ነበር፥ ዘወር ብሎም እንዲህ አላቸው። 26 ማንም ወደ እኔ የሚመጣ ቢኖር አባቱንና እናቱን ሚስቱንም ልጆቹንም ወንድሞቹንም እኅቶቹንም የራሱን ሕይወት ስንኳ ሳይቀር ባይጠላ፥ ደቀ መዝሙሬ ሊሆን አይችልም። 27 ማንም መስቀሉን ተሸክሞ በኋላዬ የማይመጣ፥ ደቀ መዝሙሬ ሊሆን አይችልም። 28 ከእናንተ ግንብ ሊሠራ የሚወድ ለመደምደሚያ የሚበቃ ያለው እንደ ሆነ አስቀድሞ ተቀምጦ ከሳራውን የማይቈጥር ማን ነው? 29 ያለዚያ መሠረቱን ቢመሠርት፥ ሊደመድመውም ቢያቅተው፥ ያዩት ሁሉ። 30 ይህ ሰው ሊሠራ ጀምሮ ሊደመድመው አቃተው ብለው ሊዘብቱበት ይጀምራሉ። 31 ወይም ሌላውን ንጉሥ በጦርነት ሊጋጠም የሚሄድ፥ ከሁለት እልፍ ጋር የሚመጣበትን በአንድ እልፍ ሊገናኝ የሚችል እንደ ሆነ አስቀድሞ ተቀምጦ የማያስብ ንጉሥ ማን ነው? 32 ባይሆንስ ሌላው ገና ሩቅ ሳለ መልክተኞች ልኮ ዕርቅ ይለምናል። 33 እንግዲህ እንደዚሁ ማንም ከእናንተ ያለውን ሁሉ የማይተው ደቀ መዝሙሬ ሊሆን አይችልም።