Amharic(i)
1 ከእናንተ አንዱ ከባልንጀራው ጋር ሙግት ቢኖረው በቅዱሳን ፊት በመፋረድ ፋንታ በዓመፀኞች ፊት ሊፋረድ ይደፍራልን? 2 ቅዱሳን በዓለም ላይ እንዲፈርዱ አታውቁምን? በዓለምስ ላይ ብትፈርዱ ከሁሉ ይልቅ ትንሽ ስለሚሆን ነገር ልትፈርዱ አትበቁምን? 3 የትዳር ጉዳይ ይቅርና በመላእክት እንኳ እንድንፈርድ አታውቁምን? 4 እንግዲህ ስለ ትዳር ጉዳይ የፍርድ ቤት ቢያስፈልጋችሁ በቤተ ክርስቲያን የተናቁትን ሰዎች ፈራጆች አድርጋችሁ ታስቀምጣላችሁን? 5 አሳፍራችሁ ዘንድ ይህን እላለሁ። እንደዚህ ነውን? በወንድሞች መካከል ሽማግሌ ሊሆን የሚችል አንድ አስተዋይ ሰው በእናንተ ዘንድ አይገኝምን?