Revelation 20:7-15

Amharic(i) 7 ሺሁም ዓመት ሲፈጸም ሰይጣን ከእስራቱ ይፈታል፥ 8 በአራቱም በምድር ማዕዘን ያሉትን አሕዛብ፥ ጎግንና ማጎግን፥ እንዲያስታቸው ለሰልፍም እንዲያስከትታቸው ይወጣል፤ ቍጥራቸውም እንደ ባሕር አሸዋ የሚያህል ነው። 9 ወደ ምድርም ስፋት ወጡ የቅዱሳንንም ሰፈርና የተወደደችውን ከተማ ከበቡ፤ እሳትም ከሰማይ ከእግዚአብሔር ዘንድ ወርዳ በላቻቸው። 10 ያሳታቸውም ዲያብሎስ አውሬውና ሐሰተኛው ነቢይ ወዳሉበት ወደ እሳቱና ወደ ዲኑ ባሕር ተጣለ፥ ለዘላለምም እስከ ዘላለም ቀንና ሌሊት ይሣቀያሉ። 11 ታላቅና ነጭ ዙፋንን በእርሱም ላይ የተቀመጠውን አየሁ፥ ምድርና ሰማይም ከፊቱ ሸሹ ስፍራም አልተገኘላቸውም። 12 ሙታንንም ታናናሾችንና ታላላቆችን በዙፋኑ ፊት ቆመው አየሁ፥ መጻሕፍትም ተከፈቱ፤ ሌላ መጽሐፍም ተከፈተ እርሱም የሕይወት መጽሐፍ ነው፤ ሙታንም በመጻሕፍት ተጽፎ እንደ ነበረ እንደ ሥራቸው መጠን ተከፈሉ። 13 ባሕርም በእርሱ ውስጥ ያሉትን ሙታን ሰጠ፥ ሞትና ሲኦልም በእነርሱ ዘንድ ያሉትን ሙታን ሰጡ፥ እያንዳንዱም እንደ ሥራው መጠን ተከፈለ። 14 ሞትና ሲኦልም በእሳት ባሕር ውስጥ ተጣሉ። ይህም የእሳት ባሕር ሁለተኛው ሞት ነው። 15 በሕይወትም መጽሐፍ ተጽፎ ያልተገኘው ማንኛውም በእሳት ባሕር ውስጥ ተጣለ።