Acts 15:27-41

Amharic(i) 27 ራሳቸውም ደግሞ በቃላቸው ያንኑ ይነግሩአችሁ ዘንድ ይሁዳንና ሲላስን ልከናል። 28 ለጣዖት ከተሠዋ፥ ከደምም፥ ከታነቀም፥ ከዝሙትም ትርቁ ዘንድ ከዚህ ከሚያስፈልገው በቀር ሌላ ሸክም እንዳንጭንባችሁ እኛና መንፈስ ቅዱስ ፈቅደናልና፤ ከዚህም ሁሉ ራሳችሁን ብትጠብቁ በመልካም ትኖራላችሁ። ጤና ይስጣችሁ። 30 እነርሱም ተሰናብተው ወደ አንጾኪያ ወረዱ፥ ሕዝቡንም ሰብስበው ደብዳቤውን ሰጡአቸው። 31 ባነበቡትም ጊዜ ከምክሩ የተነሣ ደስ አላቸው። 32 ይሁዳና ሲላስም ደግሞ ነቢያት ነበሩና ወንድሞችን በብዙ ቃል መክረው አጸኑአቸው። 33 አያሌ ቀንም ከተቀመጡ በኋላ ከወንድሞች በሰላም ተሰናብተው ወደ ሐዋርያት ሄዱ። 34 ሲላስ ግን በዚያ ይኖር ዘንድ ፈቀደ። 35 ጳውሎስና በርናባስም ከሌሎች ከብዙ ሰዎች ጋር ደግሞ የጌታን ቃል እያስተማሩና ወንጌልን እየሰበኩ በአንጾኪያ ይቀመጡ ነበር። 36 ከጥቂት ቀንም በኋላ ጳውሎስ በርናባስን። ተመልሰን የጌታን ቃል በተናገርንበት በየከተማው ሁሉ ወንድሞችን እንጐብኛቸው፥ እንዴት እንዳሉም እንወቅ አለው። 37 በርናባስም ማርቆስ የተባለውን ዮሐንስን ደግሞ ከእነርሱ ጋር ይወስድ ዘንድ አሰበ፤ 38 ጳውሎስ ግን ይህን ከእነርሱ ጋር ሊወስድ አልፈቀደም፥ ከእነርሱ ዘንድ ከጵንፍልያ ተለይቶ ነበርና፥ ወደ ሥራም ከእነርሱ ጋር አልመጣም ነበርና። 39 ስለዚህም እርስ በርሳቸው እስኪለያዩ ድረስ መከፋፋት ሆነ፥ በርናባስም ማርቆስን ይዞ በመርከብ ወደ ቆጵሮስ ሄደ። 40 ጳውሎስ ግን ሲላስን መረጠ፥ ወንድሞችም ለእግዚአብሔር ጸጋ አደራ ከሰጡት በኋላ ወጣ፤ 41 አብያተ ክርስትያናትንም እያጸና በሶርያና በኪልቅያ ይዞር ነበር።