2 Corinthians 12:1-9

Amharic(i) 1 ትምክህት የሚያስፈልግ ነው፤ አይጠቅምም ነገር ግን ከጌታ ወዳለው ራእይና መገለጥ እመጣለሁ። 2 ሰውን በክርስቶስ አውቃለሁ፥ በሥጋ እንደ ሆነ አላውቅም ወይም ከሥጋ ውጭ እንደ ሆነ አላውቅም፥ እግዚአብሔር ያውቃል፤ እንዲህ ያለው ሰው ከአሥራ አራት ዓመት በፊት እስከ ሦስተኛው ሰማይ ድረስ ተነጠቀ። 3 እንዲህ ያለውንም ሰው አውቃለሁ፥ በሥጋ እንደ ሆነ ወይም ያለ ሥጋ እንደ ሆነ አላውቅም፥ እግዚአብሔር ያውቃል፤ 4 ወደ ገነት ተነጠቀ፥ ሰውም ሊናገር የማይገባውን የማይነገረውን ቃል ሰማ። 5 እንደዚህ ስላለው እመካለሁ፥ ስለ ራሴ ግን ከድካሜ በቀር አልመካም። 6 ልመካ ብወድስ ሞኝ አልሆንም፥ እውነትን እላለሁና፤ ነገር ግን ማንም ከሚያይ ከእኔም ከሚሰማ የምበልጥ አድርጎ እንዳይቆጥረኝ ትቼአለሁ። 7 ስለዚህም በመገለጥ ታላቅነት እንዳልታበይ የሥጋዬ መውጊያ፥ እርሱም የሚጎስመኝ የሰይጣን መልእክተኛ ተሰጠኝ፤ ይኸውም እንዳልታበይ ነው። 8 ስለዚህ ነገር ከእኔ እንዲለይ ሦስት ጊዜ ጌታን ለመንሁ። 9 እርሱም። ጸጋዬ ይበቃሃል፥ ኃይሌ በድካም ይፈጸማልና አለኝ። እንግዲህ የክርስቶስ ኃይል ያድርብኝ ዘንድ በብዙ ደስታ በድካሜ ልመካ እወዳለሁ።