Revelation 19:11-21

Amharic(i) 11 ሰማይም ተከፍቶ አየሁ፥ እነሆም አምባላይ ፈረስ፥ የተቀመጠበትም የታመነና እውነተኛ ይባላል፥ በጽድቅም ይፈርዳል ይዋጋልም። 12 ዓይኖቹም እንደ እሳት ነበልባል ናቸው፥ በራሱ ላይም ብዙ ዘውዶች አሉ፥ ከእርሱም በቀር አንድ እንኳ የማያውቀው የተጻፈ ስም አለው፤ 13 በደምም የተረጨ ልብስ ተጐናጽፎአል፥ ስሙም የእግዚአብሔር ቃል ተብሎአል። 14 በሰማይም ያሉት ጭፍራዎች ነጭና ጥሩ ቀጭን የተልባ እግር ልብስ ለብሰው በአምባላዮች ፈረሶች ተቀምጠው ይከተሉት ነበር። 15 አሕዛብንም ይመታበት ዘንድ ስለታም ሰይፍ ከአፉ ይወጣል፤ እርሱም በብረት በትር ይገዛቸዋል፤ እርሱም ሁሉን የሚገዛ የእግዚአብሔርን የብርቱ ቍጣውን ወይን መጥመቂያ ይረግጣል። 16 በልብሱና በጭኑም የተጻፈበት። የነገሥታት ንጉሥና የጌታዎች ጌታ የሚል ስም አለው። 17 አንድም መልአክ በፀሐይ ውስጥ ቆሞ አየሁ፥ በሰማይም መካከል ለሚበሩ ወፎች ሁሉ። መጥታችሁ የነገሥታትን ሥጋና የሻለቃዎችን ሥጋ የብርቱዎችንም ሥጋ የፈረሶችንም በእነርሱም የተቀመጡትን ሥጋ የጌታዎችንና የባሪያዎችንም የታናናሾችንና የታላላቆችንም ሁሉ ሥጋ እንድትበሉ ወደ ታላቁ ወደ እግዚአብሔር እራት ተከማቹ ብሎ በታላቅ ድምፅ ጮኸ። 19 በፈረሱም የተቀመጠውን ጭፍራዎቹንም ይወጉ ዘንድ አውሬውና የምድር ነገሥታት ጭፍራዎቻቸውም ተከማችተው አየሁ። 20 አውሬውም ተያዘ በእርሱም ፊት ተአምራትን እያደረገ የአውሬውን ምልክት የተቀበሉትን ለምስሉም የሰገዱትን ያሳተ ሐሰተኛው ነቢይ ከእርሱ ጋር ተያዘ፤ ሁለቱም በሕይወት ሳሉ በዲን ወደሚቃጠል ወደ እሳት ባሕር ተጣሉ። 21 የቀሩትም በፈረስ ላይ ከተቀመጠው ከአፉ በሚወጣው ሰይፍ ተገደሉ፤ ወፎችም ሁሉ ከሥጋቸው ጠገቡ።