2 Corinthians 9

Amharic(i) 1 ለቅዱሳን ስለሚሆነው አገልግሎት ልጽፍላችሁ አያስፈልግምና፤ 2 በጎ ፈቃዳችሁን አውቄአለሁና፤ ስለዚህም። አካይያ ከአምና ጀምሮ ተዘጋጅቶአል ብዬ ለመቄዶንያ ሰዎች በእናንተ እመካለሁ፥ ቅንዓታችሁም የሚበዙቱን አነሣሥቶአል። 3 ነገር ግን ለእነርሱ እንዳልሁ፥ የተዘጋጃችሁ ትሆኑ ዘንድ በዚህም ነገር ስለ እናንተ ያለው ትምክህታችን ከንቱ እንዳይሆን ወንድሞችን እልካለሁ፤ 4 ምናልባት የመቄዶንያ ሰዎች ከእኔ ጋር ቢመጡ፥ ያልተዘጋጃችሁም ሆናችሁ ቢያገኙአችሁ፥ እናንተ እንድታፍሩ አላልንም እኛ ግን በዚህ እምነታችን እንድናፍር አይሁን። 5 እንግዲህ እንደ በረከት ሆኖ ከስስት የማይሆን ይህ የተዘጋጀ ይሆን ዘንድ አስቀድመው ወደ እናንተ መጥተው፥ አስቀድማችሁ ተስፋ የሰጣችሁትን በረከት አስቀድመው እንዲፈጽሙ ወንድሞችን እለምን ዘንድ እንዲያስፈልገኝ አሰብሁ። 6 ይህንም እላለሁ። በጥቂት የሚዘራ በጥቂት ደግሞ ያጭዳል፥ በበረከትም የሚዘራ በበረከት ደግሞ ያጭዳል። 7 እግዚአብሔር በደስታ የሚሰጠውን ይወዳልና እያንዳንዱ በልቡ እንዳሰበ ይስጥ፥ በኀዘን ወይም በግድ አይደለም። 8 በተነ፥ ለምስኪኖች ሰጠ፥ ጽድቁ ለዘላለም ይኖራል ተብሎ እንደ ተጻፈ፥ እግዚአብሔር፥ ሁልጊዜ በነገር ሁሉ ብቃትን ሁሉ አግኝታችሁ ለበጎ ሥራ ሁሉ ትበዙ ዘንድ፥ ጸጋን ሁሉ ሊያበዛላችሁ ይችላል። 10 ለዘሪ ዘርን ለመብላትም እንጀራን በብዙ የሚሰጥ እርሱም የምትዘሩትን ዘር ይሰጣችኋል ያበረክትላችሁማል፥ የጽድቃችሁንም ፍሬ ያሳድጋል፤ 11 በእኛ በኩል ለእግዚአብሔር የምስጋና ምክንያት የሚሆነውን ልግስና ሁሉ እንድታሳዩ በሁሉ ነገር ባለ ጠጎች ትሆናላችሁ። 12 የዚህ ረድኤት አገልግሎት ለቅዱሳን የሚጎድላቸውን በሙሉ የሚሰጥ ብቻ አይደለምና፥ ነገር ግን ደግሞ በብዙ ምስጋና ለእግዚአብሔር ይበዛል፤ 13 በዚህ አገልግሎት ስለ ተፈተናችሁ፥ በክርስቶስ ወንጌል በማመናችሁ ስለሚሆን መታዘዝ እነርሱንና ሁሉንም ስለምትረዱበት ልግስና እግዚአብሔርን ያከብራሉ፥ 14 ራሳቸውም ስለ እናንተ ሲያማልዱ፥ በእናንተ ላይ ከሚሆነው ከሚበልጠው ከእግዚአብሔር ጸጋ የተነሣ ይናፍቁአችኋል። 15 ስለማይነገር ስጦታው እግዚአብሔር ይመስገን።